ቢዝነስ

ለሞዛምቢክ የቡና ዘርፍ ባለሙያዎች በኢትዮጵያ ስልጠና እየተሰጠ ነው

By ዮሐንስ ደርበው

April 15, 2024

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሞዛምቢክ ለመጡ 12 የቡና ዘርፍ ባለሙያዎች በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የቡና ማሰልጠኛ ማዕከል ሁለተኛ ዙር ስልጠና መስጠት ተጀመረ፡፡

ሰልጣኞቹ ቀደም ሲል በባሬስታ፣ በቅምሻ እና በቡና መቁላት ዘርፎች የሰለጠኑ ሲሆን÷ በዚህኛው ዙርም በተለይም በቅምሻና ቡና መቁላት ላይ ያተኮረ ስልጠና ለመውሰድ ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ተገልጿል፡፡

በቡናና ሻይ ባለስልጣን የኢዩ ካፌ ፕሮጀክት አስተባባሪ ፍቅሩ አመኑ በስልጠናው ላይ ባደረጉት ንግግር÷ በኢትዮጵያ ከ1950ዎቹ ጀምሮ ተቋማዊ የቡና ዘርፍ እንቅስቃሴ እንደተጀመረ በመጥቀስ፤ የረጅም ጊዜ ተቋማዊ የቡና አመራር ልምድ መኖሩን አብራርተዋል፡፡

ከቡና ዘርፍ ሥራዎች ጋር በተያያዘም ባለስልጣኑ ለሞዛምቢክ ልምዱን ለማካፈልና አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ ነው ማለታቸውን የቡናና ሻይ ባለስልጣን መረጃ አመላክቷል፡፡

ማዕከሉ በተለያየ ጊዜ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለመጡ ሰልጣኞች÷ በባሬስታ፣ በቅምሻ እና በቡና መቁላት ዙሪያ ስልጠና ሲሰጥ መቆየቱ ይታወሳል፡፡