አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አንድ ሰው የደም ግፊት መጠኑ ከፍተኛ ከሆነ እና በጊዜው ሕክምና ካላደረገ ለከፍተኛ የልብ በሽታና በደም ዝውውር ማነስ ምክንያት ለሚከሰት የአዕምሮ ሥራ መታወክ (ስትሮክ) የመጋለጥ ዕድሉ እጅግ በጣም ከፍተኛ ይሆናል፡፡
በኢትዮጵያ ከጠቅላላው ሕዝብ 20 በመቶው ከፍተኛ የደም ግፊት መጠን እንዳለበትና ከእነዚህ መካከል አብዛኛዎቹ ከፍተኛ የደም ግፊት መጠን እንዳለባቸው እንደማያውቁ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሣይንስ ኮሌጅ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል መረጃ ይገልጻል፡፡
ከፍተኛ የደም ግፊት ለአጣዳፊ የልብ ውጋት ወይም በደም ዝውውር ማነስ ምክንያት ለሚከሰት የአዕምሮ ሥራ መታወክ (ስትሮክ) የመጋለጥ ዕድልን እንደሚጨምርም ተጠቁሟል፡፡
ከፍተኛ የደም ግፊት ሲኖር የህመም ስሜት ወይም ሌሎች ምልክቶች ላይታዩ እንደሚችሉም ተጠቅሷል፡፡
አንድ ሰው የደም ግፊት መጠኑ ከፍተኛ ከሆነ እና በጊዜው ሕክምና ካላደረገ ለከፍተኛ የልብ በሽታና በደም ዝውውር ማነስ ምክንያት ለሚከሰት የአዕምሮ ሥራ መታወክ (ስትሮክ) የመጋለጥ ዕድሉ እጅግ በጣም ከፍተኛ እንደሚሆን ነው የተጠቀሰው፡፡
በአብዛኛው ለከፍተኛ የደም ግፊት ተጋላጭ የሆኑትም÷ ዕድሜያቸው ከ30 ዓመት በላይ በተለይም ከ45 ዓመት በላይ የሆኑ፣ ከፍተኛ የሰውነት ክብደት ያላቸው፣ የኩላሊት በሽታ ያለባቸው፣ የስኳር በሽታ ያለባቸው፣ የደም ግፊት በሽታ በቤተሰባቸው ታሪክ ያለባቸው (በበሽታው የተጠቃ የቅርብ ዘመድ ካለ) እንዲሁም ብዙ ጊዜ የሚጨነቁ ሰዎች መሆናቸው ተብራርቷል፡፡
በተጨማሪም የሰውነት እንቅስቃሴ የማያዘወትሩ፣ ሲጋራ የሚያጨሱ ወይም አደንዛዥ እጽ የሚጠቀሙ፣ የአልኮል መጠጥ የሚያዘወትሩ፣ ብዙ ጊዜ ጨው የበዛበት ምግብ የሚመገቡ፣ በቂ ፍራፍሬና አትክልት የማይመገቡ ሰዎች ለከፍተኛ የደም ግፊት እንደሚጋለጡ ተገልጿል፡፡
በመሆኑም የደም ግፊትን በየጊዜው መለካትና መከታተል እንደሚገባ የሕክምና ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡