የሀገር ውስጥ ዜና

ተተኪ ስፖርተኞችን ለመፍጠር በክልሎች የሚካሄዱ ውድድሮች ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ

By Tamrat Bishaw

April 14, 2024

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጅራ በክልሎች የሚደረጉ ውድድሮች ተተኪ ስፖርተኞችን በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ አስተዋኦ እንዳላቸው ገለጹ፡፡

የኦሮሚያ ክልል ሁሉም ዞኖች እና 26 ከተሞች የሚሳተፉበት 26ኛው አጠቃላይ የስፖርት ሻምፒዮና በጅማ ከተማ መካሄድ ጀምሯል፡፡

አቶ ኢሳያስ በጅማ ከተማ በተካሄደው የማስጀመሪያ መርሐ-ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር÷ መሰል ውድድሮች ተተኪ ስፖርተኞችን በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ አስተዋኦ እንዳላቸው አስገንዝበዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ማቲዎስ ሰቦቃ በበኩላቸው÷ ውድድሩ ወንድማማችነትን እንደሚያጠናክር አስረድተዋል፡፡

ዛሬ የተጀመረው ሻምፒዮና በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች እየተካሄደ ለሁለት ሳምንታት እንደሚቆይ ተገልጿል።

በሙክታር ጠሃ እና በአብዱራህማን መሐመድ