የሀገር ውስጥ ዜና

4ኛው የፋና ላምሮት የአሸናፊዎች አሸናፊ የፍጻሜ ውድድር ዛሬ በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ይካሄዳል

By Shambel Mihret

April 13, 2024

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው 4ኛው የአሸናፊዎች አሸናፊ የፋና ላምሮት የፍጻሜ ውድድር ዛሬ በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ይካሄዳል።

ላለፉት 12 ሳምንታት በ16 ተወዳዳሪዎች መካከል ሲደረግ የነበረው የአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር በዛሬው ዕለት በ13ኛ ሳምንቱ ከአራት ምርጥ የፍጻሜ ተወዳዳሪዎች ጋር ፍጻሜውን ያደርጋል።

ለዚህ ደማቅ የፍጻሜ ዝግጅት የደረሱት አራቱ ድንቆች ትዕግስት አስማረ፣ ሄኖክ ብርሃኑ፣ በአምላክ ቢያድግልኝ እና ሃብታሙ ይሄነው ልዩ ዝግጅት አድርገዋል።

በዚህ ተጠባቂ የፍጻሜ ውድድር ላይ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ባለውለታ የሆኑ ሁለት አንጋፋ ሙዚቀኞች በእንግድነት ይገኛሉ።

ተወዳዳሪዎች ራሳቸው ከተዘጋጁባቸው ሙዚቃዎች በተጨማሪ ለፍጻሜው በተዘጋጀ አዲስ እና ወጥ ሙዚቃም ይወዳደራሉ፡፡

በውድድሩ 1ኛ ደረጃን ይዞ ለሚያጠናቅቅ አሸናፊ የ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የገንዘብ ሽልማትና የፋና ላምሮት የክብር ዋንጫ ተዘጋጅቷል።

ከ2ኛ እስከ 4ኛ ደረጃን ይዘው ለሚያጠናቅቁ ተወዳዳሪዎችም ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደየደረጃቸው የገንዘብ ሽልማት የሚያበረክት ይሆናል፡፡

በአጠቃላይ ለ4ኛው የፋና ላምሮት የአሸናፊዎች አሸናፊ የፍጻሜ ውድድር የ3 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር ሽልማትተዘጋጅቷል።

ከ2011 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ መድረክ ያጡ ድምጻውያንን መድረክ እንዲያገኙ ያስቻለው የፋና ላምሮት ውድድር ከሚያስገኘው የገንዘብ ሽልማት በላይ ለተወዳዳሪዎች ቀጣይ የሙዚቃ ጉዞ መንገድ እየከፈተ ይገኛል።

ከሁሉም በላይ ደግሞ ተወዳዳሪዎች በአድማጭ ተመልካች ዘንድ እውቅና እንዲያገኙ በማገዝ ብዙዎችን እያነቃቃ ነው።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አድማጭ ተመልካቹ የዛሬውን የፍጻሜ ውድድር በፋና ቴሌቪዥን፣ በፋና የፌስቡክ እና የቴሌግራም ገጾችን ጨምሮ በ www.fanabc.com ከ5፡30 ጀምሮ በቀጥታ ሥርጭት በመከታተል በ8222 አጭር የጽሑፍ መልዕክት የተወዳዳሪዎችን ኮድ በመላክ እየተዝናና እንዲደግፍ ጋብዟል፡፡

በለምለም ዮሐንስ