የሀገር ውስጥ ዜና

ብሪታንያ ለቀድሞ ታጣቂዎች መልሶ ማቋቋም ሥራ የምታደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ

By Mikias Ayele

April 12, 2024

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ እየተከናወነ የሚገኘው የቀድሞ ታጣቂዎች መልሶ ማቋቋም ሥራ ስኬታማ እንዲሆን የብሪታንያ መንግሥት የሚያደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አምባሳደር ዳረን ዌልች አረጋገጡ፡፡

የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን በኢትዮጵያ የብሪታንያ አምባሳደር ከሆኑት ዳረን ዌልች ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም÷ ኮሚሽኑ የተሰጠውን ተልዕኮ ለማሳካት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትንና ያጋጠሙ ችግሮችን ኮሚሽነር ተመስገን አብራርተዋል፡፡

የብሪታንያ መንግሥት ለመርሐ-ግብሩ ማስፈፀሚያ ላደረገው የገንዘብ ድጋፍ አመስግነው÷ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቃቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

አምባሳደር ዳረን በበኩላቸው ኮሚሽኑ እያከናወነ ያለውን ሥራ አድንቀው÷ የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ በማቋቋም ሂደት የብሪታንያ መንግሥት የሚያደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡