አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ ከኢራን ጥቃት ሊሰነዘር ይችላል በሚል ስጋት በእስራኤል ያሉ ዲፕሎማቶቿ ላይ የጉዞ ክልከላ ማድረጓ ተገለጸ፡፡
በእስራኤል የአሜሪካ ኤምባሲ፤ ለጥንቃቄ ሲባል ዲፕሎማቶቹ ከእየሩሳሌም፣ ከቴልአቪቭ ወይም ከቤርሳቤህ አከባቢዎች ውጭ እንዳይጓዙ ማሳሰቡ ተመላክቷል።
ኢራን ከ11 ቀናት በፊት በሶሪያ በሚገኘው ቆንስላዋ ላይ በደረሰ ጥቃት ለ13 ሰዎች ህይወት መቀጠፍ እስራኤልን በመወንጀል አጸፋውን ለመመለስ መዛቷ ይታወሳል።
የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን ከኢራን አቻቸው ጋር በስልክ ባደረጉት ውይይት ውጥረት የሚጨምር የአጸፋ እርምጃ እንዳይወሰድ መጠየቃቸው ተመላክቷል።
እስራኤል ቆንስላ ጽህፈት ቤቱ ላይ ለደረሰው ጥቃት ኃላፊነቱን ባትወስድም፤ ከጥቃቱ ጀርባ እንደነበረች ግን በስፋት እንደሚታመን ቢቢሲ ዘግቧል።
ጥቃቱ የደረሰው በጋዛ ያለው ጦርነት በአካባቢው እንዳይስፋፋ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች እየተደረጉ ባለበት ወቅት ነው።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከትናንት በስቲያ ባደረጉት ንግግር ኢራን ግልፅ ጥቃት እንደምትፈጽም በማስጠንቀቅ ለእስራኤል ብረት ለበስ ድጋፍ ለመስጠት ቃል ገብተዋል።