አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ የደም ካንሰር አይነቶች ያሉ ሲሆን በዋናነት ብዙ ጊዜ በህፃናት ላይ በመከሰት የሚታወቀው ‘አኪውት ሊምፎብላስቲክ ሉኪሚያ’ ነው።
ሁለተኛው በህፃናት ላይ የሚከሰት የደም ካንሰር ‘አኪውት ማይሎጂነስ ሉኪሚያ’ ነው።
እነዚህ ሁለት የካንሰር አይነቶች የሚነሱት ከነጭ የደም ህዋሳት ነው፤ አኪውት ሊምፎብላስቲክ ሉኪሚያ የሚነሳው ሊንፎሳይት ከሚባለው ነጭ የደም ህዋስ ሲሆን÷ አኪውት ማይሎጂነስ ሉኪሚያ ደግሞ ማይሎድ ከሚባለው ነጭ የደም ህዋስ ይነሳል።
እነዚህ ህዋሳት ትክክለኛውን የእድገት ዑደት ሳይጨርሱ ጤነኛ ወዳልሆነ ህዋስነት በመቀየር መቅኔ ውስጥ በመራባት ለሰውነት የሚያስፈልጉ ጤነኛ እና ጠቃሚ የደም ህዋሳት በበቂ መጠን እንዳይመረቱ ያደርጋሉ።
በዚህም ጤነኛ የሆኑ ነጭ የደም ህዋሳት በበቂ መጠን እንዳይመረቱ ስለሚያደርጉ የኢንፌክሽን ተጋላጭነትን ይጨምራሉ።
ኢንፌክሽን ሲኖር ትኩሳትን ጨምሮ የተለያዩ ምልክቶች ይታያሉ። እንዲሁም ደም እንዳይፈስና እንዲረጋ የሚያደርገውን “ፕላትሌት” የተሰኘው የደም ህዋስ በበቂ መጠን እንዳይመረት ስለሚያደርጉ፤ በዚህ በሽታ የተጠቃ ህፃንም ሆነ አዋቂ የተለያየ የሰውነት ክፍል ላይ መድማት ሊያጋጥም ይችላል።
ጭንቅላት፣ ሆድ ዕቃ፣ ሽንት ቧንቧ፣ ወዘተ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ላይ ቢደማ ምልክቱ በተለያየ መልክ ሊገለጥ ይችላል፤ ለአብነትም ቆዳ ውስጥ ቢደማ መበለዝ፣ ቀይ ነጠብጣብ፣ የመሳሰሉ ምልክቶች ይስተዋላሉ።
ሌላው እነዚህ የካንሰር ህዋሳት ከመቅኔ ወጥተው ወደ ተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ሲሰራጩና ሲከማቹ ደግሞ የተለያዩ ምልክቶችን ያሳያሉ፤ በተለይ አኪውት ሊምፎብላስቲክ ሉኪሚያ ወደ ጭንቅላት ሲሰራጭ ራስ ምታት፣ ደም ግፊት፣ ማስታወክ፣ ማንቀጥቀጥ ወዘተ የመሳሰሉ ምልክቶች ሊኖር ይችላል፤ በወንዶች የዘር ፍሬ ላይ ሲቀመጥ ደግሞ የወንድ ፍሬ ማበጥ ይስተዋላል።
በተጨማሪም አኪውት ሊምፎብላስቲክ ሉኪሚያ የደም መፍሰስ፣ የአጥንት ወይም የመገጣጠሚያ ህመም እና ከመጠን በላይ ላብ ሊያስከትል ይችላል።
በህፃናት ላይ የሚከሰቱት ሁለቱም የደም ካንሰሮች ተመሳሳይ ምልክት ያላቸው ሲሆን÷ ድካም፣ በተደጋጋሚ ለኢንፌክሽንና ለደም ማነስ በሽታ መጋለጥ፣ መድማት፣ ክብደት መቀነስ፣ ትኩሳት፣ የሆድ እብጠት፣ ራስ ምታት የመሳሰሉ ምልክቶች ይስተዋላሉ።
ስለዚህ በሽታዎቹ የሚለዩት የመቅኔ ምርመራ በማድረግ እንደሆነ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።
የአብዛኞቹ የደም ካንሰሮች ትክክለኛ መንስኤ ምን እንደሆነ ባይታወቅም ሁሉም የደም ካንሰሮች ጤነኛ ያልሆኑ የደም ህዋሳት መቅኔ ውስጥ በመራባታቸው ሳቢያ የሚከሰቱ መሆናቸው ይገለፃል፡፡
ሆኖም በዘር የሚመጡ ችግሮች፣ ብዙ የጨረር ሕክምና በመውሰድ፣ አንዳንድ የቫይረስ ኢንፌክሽኖች (ማለትም ኤችአይቪ፣ ኢፒስቲን ባር ቫይረስ) ለደም ካንሰር ሊያጋልጡ ይችላሉ።
ማስተዋል ያለብን ነገር አንዳንድ ምልክቶች ከሌላ ህመም ምልክቶች ጋር ሊመሳሰሉ ስለሚችሉ ወላጆች ከላይ የተጠቀሱ ምልክቶችን ህጻናት ላይ ሲያዩ በፍጥነት ወደ ጤና ተቋም በመውሰድ በጊዜ ሊያስመረምሩ እንደሚገባ ይመከራል፡፡
ህመሙ ልክ እንደሌሎች ህመሞች ታክሞ እንደሚድን መገንዘብም ያስፈልጋል፡፡