አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ተወዳዳሪና ለምጣኔ ሀብታዊ እድገት አስተዋፅኦ የሚያበረክት የንግድ ዘርፍ ለመፍጠር በጥናት የተደገፈ የብድር አቅርቦት ማመቻቸት እንደሚገባ የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ገለጸ፡፡
የብድር አቅርቦት በቢዝነስ ስራዎች ላይ ስላለው ተፅዕኖ የሚወያይ መድረክ የንግዱ ማህበረሰብ፣ የብሄራዊ ባንክና የፋይናንስ ተቋማት ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ እየተካሄደ ነው።
የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት መሰንበት ሸንቁጤ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት÷ ለምጣኔ ሀብት እድገት የንግዱ ማህበረሰብ ሚና ከፍተኛ ነው።
በዚህም ምክር ቤቱ የግሉን ዘርፍ በማጠናከር በሀገራችን ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ የበኩሉን ሚና እየተወጣ ነው ብለዋል።
የተጠናከረ የንግድ ማህበረሰብ ከመፍጠር አንፃር ግን በርካታ ተግዳሮቶች መኖራቸውን ገልጸው፤ የብድር አቅርቦት ተግዳሮት ሰፊውን ድርሻ እንደሚይዝ አመልክተዋል።
በተለይም ለግሉ ዘርፍ የሚሰጠው የብድር መጠን በቂ አለመሆን፣ ለብድር የሚጠየቀው ማስያዣ አለመመጣጠን፣ የብድር መመለሻ ጊዜ አነስተኛ መሆን፣ ለጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች ተመጣጣኝ ወለድ ያለው የብድር አቅርቦት ከመፍጠር አንፃር የሚሉትን እንደተግዳሮት አንስተዋል፡፡
በመሆኑም እነዚህን ችግሮች በመፍታት በባንኮችና ማይክሮ ፋይናንሶች ፖሊሲና መመሪያን መሰረት ያደረገ የብድር አቅርቦት እንዲፈጠር መንግስት በትኩረት መስራት እንዳለበት ተናግረዋል።
በሳሙኤል ወርቃየሁ