Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በረመዳን ወር የታየዉ የመተሳሰብና የመረዳዳት ተግባር ቀጣይነት ሊኖረዉ ይገባል – አቶ እንዳሻው ጣሰው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በረመዳን ወር የታየዉ የመተሳሰብ፣ ተካፍሎ የመብላትና የመረዳዳት ተግባር ቀጣይነት ሊኖረዉ እንደሚገባው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው አስገነዘቡ።

ም/ርዕሰ መስተዳድሩ ለእስልምና እምነት ተከታዮእ እንኳን ለ1 ሺህ 445ኛው የዒድ አል-ፈጥር በዓል አደረሳችሁ ሲሉ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም÷ የዘንድሮው የረመዳን ወር ፆም በየአካባቢያችን በጋራ የኢፍጣር ስነ ስርዓቶች አጅበን የተጓዝንበት ድባብ ልዩ ትውስታ አለው ብለዋል፡፡

‘ብዝሃነታችን ውበታችንና በረከታችን ነዉ’ የሚለዉን መንፈስ መሠረት አድርገን የኢፍጣር ማዕዶችን በህብረት መቋደሳችን አብሮነታችን የሚያጠናክር ነው ሲሉም ገልጸዋል።

በረመዳን ወር የታየዉ የመተሳሰብ፣ ተካፍሎ የመብላትና የመረዳዳት ተግባርም ቀጣይነት ሊኖረዉ እንደሚገባው አመልክተዋል።

ኢትዮጵያዊነት በፈሪሀ ፈጣሪ በረከት የተሞላ፣ መንፈሳዊና ሞራላዊ እሴት የገነባው በወንድም/እህትማማችነት እሴት ላይ የተመሠረተ መሆኑን መግለጻቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ያመረጃ አመላክቷል፡፡

አብሮነትን የሚያፀኑ ዘመን ተሻጋሪ መስተጋብሮች ያስተሳሰሩን ሕዝቦች ነን ያሉት አቶ እንዳሻው ጣሰው፤ በጋራ እዉነቶች፣ ፍላጎቶችና ጥቅሞች ላይ የተመሠረት ትርክትን ለማስረፅና ለማፅናት ኃላፊነታችንን እንወጣ ብለዋል በመልዕክታቸው።

Exit mobile version