Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የዒድ አል-ፈጥር በዓል የመተሳሰብ፣ የመጠያየቅ፣ የመረዳዳትና የአብሮነት በዓል ነው – አቶ ጥላሁን ከበደ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዒድ አል-ፈጥር በዓል የመተሳሰብ፣ የመጠያየቅ፣ የመረዳዳትና የአብሮነት በዓል መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ÷ 1 ሺህ 445ኛውን የዒድ-ፈጥር በዓልን አስመልክቶ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት÷ በዓሉ በእስልምና እምነት ተከታዮች ልዩ ትርጉም ያለው የቅዱሱ የረመዳን ወር ማሳረጊያ ታላቅ በዓል ነው ብለዋል፡፡

ዕለቱ ሕዝበ ሙስሊሙ በቅዱሱና በታላቁ የረመዳን ወር ለኢትዮጵያ ሰላምና ፀጋ፣ ለህዝቡ ፍቅርና አንድነት ወሩን ሙሉ በፆምና በዱአ አሳልፎ ከፈጣሪ እዝነትና በረከት የሚቀበልበት ልዩ ቀን መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የዒድ አል-ፈጥር በዓል የመተሳሰብ፣ የመጠያየቅ፣ የመረዳዳትና የአብሮነት በመሆኑ ሕዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ወቅት ሲያደርገው እንደነበረው በአንድነት ተሰባስቦ ያለው ለሌለው በማካፈል ማህበራዊ ትስስሩን ይበልጥ አጠንክሮ በአብሮነት እንደሚያከብረው ገልጸዋል፡፡

አንድነትና ኅብረት፣ መደጋገፍና መረዳዳት በእስልምና ልዩ ስፍራ እንደሚሰጠው የእምነቱ አስተምህሮ ያስረዳል ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን ከሚያለያዩን ነገሮች ይልቅ አንድ የሚያደርጉን የበርካታ ዕሴቶች ባለቤት የሆንን ህዝቦች ብቻ ሳንሆን ልዩነቶቻችን የኅብር ማንነትን ውበት ያጎናፀፉን ድንቅ ህዝቦች ነን ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡

ህዝበ ሙስሊሙ የእምነቱ አስተምህሮ በሚያዘውና በሚፈቅደው መሰረት በመተጋገዝና አብሮ በመስራት ለዘላቂ ሰላም፣ ዕድገት እና ሁለንተናዊ ብልፅግና ይበልጥ መትጋት እንደሚገባው አንስተዋል፡፡

በዓሉን ሲከበር የመቻቻል፣ የአብሮነት፣ የመከባበር እና የመደጋገፍ እሴትን በማጠናከር ሀገራዊ የለውጥ ጉዞን ከዳር ለማድረስ ሁሉም በየተሰማራበት በሐቅ በማገልገል የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

 

 

Exit mobile version