ፋና ስብስብ

የዒድ በዓል አከባበር በተለያዩ የዓለም ሀገራት

By Feven Bishaw

April 09, 2024

 

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)ኢድ አልፈጥር የታላቁ የረመዳን ወር መጨረሻ፤ በመላው አለም የሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች በድምቀት ያከብሩታል፡፡

የእምነቱ ተከታዮች በዕለቱ ወደ አደባባይ በመውጣት የዒድ ሶላትን በጋራ ይሰግዳሉ፣ ለረመዳን በሰላም መጠናቀቅም ፈጣሪያቸውን ያመሰግናሉ፣ ለቀጣይ ዓመት በሰላም ለመድረስም ጸሎት ይደረጋል፡፡

ያለው ለሌለው ማካፈልና ቀኑን በደስታና በጋራ ማሳለፍ ዋነኛው የበዓሉ መልዕክት ነው፡፡

የእስልምና እምነት ተከታይ በሚበዛባቸው ሀገራት ዒድ አልፈጥር በተለምዶ ለሦስት ቀናት የሚከበር ሲሆን እንደየሀገራቱ የበዓሉ ቀናት ቁጥር ሊለያይ ይችላል፡፡

ይህ ልዩ በዓል ጣፋጭ ዒድ በመባል የሚታወቅ ሲሆን÷ በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ ከዒድ ሶላት በፊት ጣፋጭ መብላት የተለመደ ነው፡፡

በተለይም በእነዚህ አካባቢዎች ከቴምር እና ሌሎች ጣፋጭ ነገሮች የተሰሩ “ማሙል” በመባል የሚታወቁ ብስኩቶችን መመገብ የተለመደ ተግባር ነው፡፡

በአብዛኞቹ ሀገራት አብዛኛውን ጊዜ ሙስሊሞች የዒድ ቀንን ጣፋጭ ነገሮችን በመያዝ ከቤት ቤት እየተዘዋወሩ ዘመዶቻቸውንና ጎረቤቶቻቸውን በመጠየቅ ያሳልፋሉ፡፡

በዒድ አልፈጥር ወቅት በጎረቤት ሀገር ሶማሊያ የዓመቱ ትልቅ ገበያ የሚገበይበት ሲሆን÷ ከምግብ ሸቀጥ ጀምሮ የአልባሳትና ሌሎች ቁሳቁሶች ገበያ ይደራል፡፡

በበዓሉ ዋዜማ የሶማሊያ ሴቶች ፋሽን ልብሶችን ይገዛሉ የመዋቢያ ቁሳቁሶችና የሽቶ ገበያውም የበለጠ ይጧጧፋል፡፡

በዕለቱ በመስጊዶች ከሚደረገው የዒድ ሶላት መልስ ዋነኛው የበዓል አከባበር የሚጀምር ሲሆን÷ በየቤቱ የተዘጋጁ ለሆ፣ ባጊያ፣ ሃኒድ እና የመሳሰሉ ምግብ ዓይነቶች በጋራ ይመገባሉ፡፡

በዚህ ማዕድ ለመካፈል ዝምድና ወይም መተዋወቅ አይጠይቅም፤ እግሩ ያደረሰው እንግዳ ሁሉ የማዕዱ ተጋሪ ነው፡፡

ከቀማመሰ በኋላም “ዒድ ዋንአክሰን” ብሎ ይሰናበታል መልካም በዓል እንደማለት ነው፡፡

የዒድ አልፈጥር በዓልን በድምቀት የምታከብረው ሌላዋ አፍሪካዊት ሀገር ደግሞ ሞሮኮ ናት፤ በሞሮኮ የበዓሉ ቀን ጠዋት ሁሉም ወንዶች ወደ መስጂድ ይሄዱና የዒድ ሶላት ይሰግዳሉ ሴቶቹ ደግሞ በቤታቸው ሆነው መለዌ እና በሃንግሃሪ የተባሉ ጣፋጭ ባህላዊ ምግቦችን ያሰናዳሉ፡፡

ወንዶች ከመስጂድ እንደተመለሱ የተዘጋጀውን ይመገባሉ፤ ከዚህ በመቀጠልም ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ መጠያየቅ በሞሮኮ የተለመደ ነው፡፡

የዒድ ቀንን በሞሮኮ ውስጥ ሁሉም የተቸገሩ ሰዎች ይጠየቃሉ፤ የታመሙትን በሆስፒታል ተገኝቶ መጠየቅ፣ የታሰሩትን መጎብኘት፣ በድህነት ውስጥ ያሉትን ማብላት፣ የተከፋን ማስደሰት የሞሮኮውያን የዒድ አልፈጥር በዓል ዋነኛ ተግባር ነው፡፡

ዒድ አልፈጥርን በፓኪስታን በተለይም ሴቶች በሂና መድመቃቸው ልዩ ያደርገዋል፤ ሂና ሴቶች በእጅና በእግሮቻቸው ላይ በደማቁና በተለያየ ቅርፅ የሚቀቡት መዋቢያ ነው፡፡

ሂና በፓኪስታናውያን በስፋት ይለመድ እንጂ በተለያዩ ሀገራት ጥቅም ላይ የሚውል መዋቢያ ነው፡፡

በዒድ አልፈጥር ዕለት ጠዋት ሁሉም የፓኪስታን ወንዶች ወደ መስጂድ ይሄዱና በዚያው የጸሎት ስነ ስርዓት ይካሄዳል፤ ጸሎቱ እንደተጠናቀቀም ወጣቶች ስጋ ለማረድ ዝግጁ ሆነው በመስጂዱ ዙሪያ ይጠባበቃሉ፡፡

ወዲያውኑ የእርድ እንሰሳት በግልም ሆነ በቡድን ያዘጋጁ ሰዎች ወደ መስጂዱ ይመጣሉ፤ የተዘጋጁ ወጣቶች እርዱን አከናውነው ሁሉንም ካዘጋጁ በዚያ ሰፈር የሚገኙ አቅመ ደካሞች ጭምር ተሰብስበው በጋራ ይመገባሉ፡፡

መምጣት ላልቻሉ ደግሞ እየተቋጠረ ይላክላቸዋል፤ ከምግብ በኋላ በሂና የተዋቡ የፓኪስታን ሴቶች በመዘዋወር ዒድ ሙባረክ እያሉ በዓሉን ያደምቁታል፡፡

በዒድ አልፈጥር ዕለት ሰዎች የበዓል መልካም ምኞት መግለጫዎቻቸውን በተለያየ መልኩ ይገልፃሉ፡፡

በብዛት ጥቅም ላይ ከሚውሉት የመልካም ምኞት መግለጫዎች ውስጥም “ዒድ ሙባረክ” የተባረከ ዒድ ወይም “ዒድ ሰዒድ” መልካም ዒድ የሚሉት ተወዳጅ እና በስፋት ጥቅም ላይ የሚውሉ ናቸው፡፡