የሀገር ውስጥ ዜና

በ2ኛ ዙር ወደሀገር ለሚገቡ 2ኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን አቀባበል እየተደረገ ነው

By Amele Demsew

April 09, 2024

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) እስከ ሚያዝያ 30 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆየው በሁለተኛ ዙር ወደ ሀገር ለሚገቡ 2ኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን አቀባበል እየተደረገ ነው።

በዛሬው ዕለት ወደ ሀገራቸው ለመጡ 2ኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቀባበል ተደርጓል።

በአቀባበል ስነስርዓቱ ላይ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታዎች ሌንሳ መኮንን እና ስለሺ ግርማን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት የስራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል::

ኢትዮጵያውያኑ “ታሪካዊ መሰረትዎን ይወቁ” በሚል በተሰየመው በሁለተኛ ዙር መርሐ ግብር ወደ ሀገር እየገቡ ሲሆን ይህም እስከ ሚያዚያ 30 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚቆይ ተጠቁሟል፡፡

በዚህኛው ምዕራፍ ኢትዮጵያውያን የእረፍት ጊዜያቸውን ተጠቅመው የሀገራቸውን ታሪክ እንዲያውቁ፣ አያቶቻቸውና ቅድመ አያቶቻቸው ለሀገር የከፈሉትን መስዋዕትነት እንዲያውቁ መዘጋጀቱን ከቱሪዝም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በቀጣይ ቀናት በተለይም የዓድዋ ድል ታሪክን ለሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ለማሳወቅ ያለመ እና ታሪኩን በመፃፍ ጭምር ለሌላው አለም ማካፈል እንዲችሉ ለማድረግ ውይይት የሚደረግበት ፓናል ውይይት እንደሚካሄድ ተገልጿል።

በተጨማሪም 16 በዩኔስኮ የተመዘገቡ የቱሪስት መስህቦችን በዲጂታል አማራጭ የሚያስተዋውቁ መርሐግብሮች እንደሚካሄዱ ተጠቁሟል።