Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኪንታሮት ህመም መዘዞችና ህክምናው

 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኪንታሮት ህመም በፊንጢጣ ላይ የሚገኙ ደም መላሽ የደም ስሮች ሲያብጡ የሚፈጠር ህመም ነው፡፡

ህመም የሌለው ከፊንጢጣ የሚፈስ ደማቅ ቀይ ደም፣ በፊንጢጣ አካባቢ ማሳከክ፣ ከፊንጢጣ የወጣ ሥጋ መሳይ እባጭና በፊንጢጣ አካባቢ የህመም ስሜት መኖር የኪንታሮት ህመም ምልክቶች ናቸው፡፡

የኪንታሮት ህመም መዘዞች፡- ኪንታሮቱ ውስጥ የደም መርጋትና ከፍተኛ ሕመም፣ ወጥቶ አለመመለስና መበስበስ፣ መመርቀዝና መግል መቋጠር፣ ያልተለመደ የሰውነት ክፍተት፣ የሰውነት መሰንጠቅ፣ ሰገራን አለመቆጣጠር፣ የተለመደ ባይሆንም የደም ማነስ ሊያስከትል ይችላል፡፡

ኪንታሮት እንዴት ይታከማል?

በመጀመሪያ ሕመሙ ያለበት ሰው እንደማንኛውም ሕመም ወደ ሐኪም ቤት ሄዶ ለመታከም ፍርሃትን/ሐፍረትን ማስወገድ ይጠበቅበታል፡፡

በተጨማሪ በፋይበር የበለፀጉ ምግቦችን (አትክልትና ፍራፍሬ…) መመገብ፣ ፈሳሽ በበቂ ሁኔታ መውሰድ፣ ለብ ባለ ውሃ ጨው ጨምሮ ከ20 እስከ 30 ደቂቃ በቀን ሁለቴ ወይም ሦሥቴ መዘፍዘፍ (በበረዶም ሊሆን ይችላል)፣ ሁልጊዜ ከተፀዳዱ በኋላ በንጹሕ ውሃ መታጠብ፣ ሻካራ የመፀዳጃ ወረቀቶችን አለመጠቀም አስፈላጊ ነው፡፡

እንዲሁም የሰገራ ማለስለሻ መድኃኒት፣ የሚቀቡ የሕመም ማስታገሻ መድኃኒት መጠቀም (በሀኪም ትዕዛዝ መሰረት) ተገቢ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜም ከላይ በተጠቀሰው መንገድ ብቻ ሕመሙ ሊሻሻልና ሊጠፋ ይችላል፡፡

በእነዚህ ሕክምናዎች ካልተስተካከለ ደግሞ ቀለል ያለ ቀዶ ሕክምና ሊያስፈልግ እንደሚችል ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኪንታሮት ህመም መከላከያ መንገዶች ምንድናቸው?

በፋይበር የበለፀጉ ምግቦችን መመገብ፣ ፈሳሽ በበቂ ሁኔታ መውሰድና የሆድ ድርቀትን ማስወገድ፣ ሰገራ በሚመጣ ጊዜ ጊዜውን ሳያሳልፉ ወደ ሽንት ቤት መሄድ፣ መፀዳጃ ቤት ለረጅም ሰዓት አለመቀመጥ ይጠቀሳሉ፡፡

Exit mobile version