አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ወረባቦ ወረዳ ቢስቲማ ከተማ፣ ሰሜን ሸዋ ዞን መሐል ሜዳ ከተማ እና ደቡብ ወሎ ዞን መቅደላ ወረዳ ማሻ ከተማ ተካሂዷል፡፡
በሰልፉ ለክልላችን ሰላም በህብረት እንቆማለን፣ በጥቂት ፅንፈኛ ኃይሎች አስተሳሰብና እኩይ ድርጊት የሚበተን ሀገርና ህዝብ የለንም፣ ክልላችንን በዉክልና ጦርነት ማፍረስ አይቻልም፣ እኛ ኢትዮጵያዊያን ለሀገራችን ሠላምና ሁለንተናዊ ብልፅግና የበኩላችንን እንወጣለን የሚሉ እና ሌሎች መልዕክቶች ተላልፈዋል።
በተጨማሪም ሀገራዊ ለውጡ ኢትዮጵያን የታደገ እና ህልውናችንን ያስቀጠለ ነው፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአንድነታችን እና የጥንካሬችን መገለጫ ነው፣ ዉስጣዊ ሠላማችንን በማፅናት ዉጫዊ ተፅዕኖዎችን በድል እንወጣለን፣ የክልላችንን አንፃራዊ ሠላም በአጭር ጊዜ ወደ ዘላቂ ሠላም እናሸጋግረዋለን የሚሉ መፈክሮች ድምጾች ተሰምተዋል፡፡
የሰልፉ ተሳታፊዎች ጉድለቶችን በማረም በለውጡ የተገኙ ድሎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ከለውጡ አመራር ጋር በፅናት መቆም እንደሚገባም ማመላከታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡