አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሞዛምቢክ ሰሜናዊ የባህር ዳርቻ በተከሰተ የጀልባ መስጠም አደጋ ከ90 በላይ ሰዎች ሕይወት አለፈ፡፡
በሞዛምቢክ የናምፑላ ግዛት ባለስልጣናት÷ ጀልባዋ 130 የሚሆኑ ሰዎችን አሳፍራ እንደነበርና ከአደጋውም አምስት ሰዎች መትረፋቸውን ተናግረዋል፡፡
ከሟቾቹ መካከል በርካታ ህፃናት እንደሚገኙ የተናገሩት የናምፑላ ዋና ፀሐፊ ጄይም ኔቶ÷ ሰዎቹ የኮሌራ ወረርሽኝን ሸሽተው እየሄዱ እንደነበር አንስተዋል፡፡
ጀልባዋ በተሳፋሪ ተጨናንቃ እንደነበር እና መንገደኞችን ለመጫን ምቹ እንዳልነበረችም ነው ዋና ፀሐፊው የገለጹት፡፡
ጀልባዋ ከሉንጋ ናምፑላ የባህር ዳርቻ ወደ ሞዛምቢክ ደሴት በመጓዝ ላይ እንደነበረችም ቢቢሲ በዘገባው አመልክቷል፡፡
ናምፑላ ግዛት ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ በተከሰተ የኮሌራ ወረርሽኝ ክፉኛ የተጠቃች ሲሆን÷ በሀገሪቱ የተከሰተው ወረርሽኝ ከ25 ዓመታት ወዲህ አስከፊ ነው ተብሏል፡፡