አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአንጀት ቁስለት በሽታ የምግብ መፍጫ ሥርዓትን አዋኪ መሆኑን የሕክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
በሽታው በየትኛውም የዕድሜ ክልል በሚገኙ ሰዎች ላይ የሚከሰት ሲሆን÷ በተለይም በወጣትነትና ጎልማሳነት ዕድሜ ባሉ ሰዎች ላይ በስፋት እንደሚከሰት ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡
የአንጀት ቁስለት በሽታ መንስኤ ምንድን ነው? • በሽታው በምን ምክንያት እንደሚከሰት በትክክል ባይታወቅም÷ የዘር ተጋላጭነት፣ የአኗኗር ሁኔታዎች እና አንጀት ውስጥ የሚገኝ ባክቴሪያ የሚሉት ሳይንሳዊ መላምቶች በመንስኤነት ይተቀሳሉ፡፡
የአንጀት ቁስለት በሽታ አይነቶች • የአንጀት ቁስለት በሽታ አይነቶች ክሮንስ እና አልሰሬቲቭ ኮላይትስ በመባል ይታወቃሉ፡፡
ክሮንስ የትኛውንም የአንጀት ክፍል (ከአፍ እስከ ፊንጢጣ ሊጎዳ ይችላል)፤ አብዛኛውን ጊዜ የትንሹን አንጀት የመጨረሻ ክፍል (የቀጭን አንጀትን ጫፍ) እና ትልቁ ን አንጀት ያጠቃል፡፡
የክሮንስ በሽታ ምልክቶችም የሆድ ህመም፣ ክብደት መቀነስ፣ ድካም እና የሰገራ መልክ መቀየር ናቸው፡፡
ክሮንስ ሙሉ የአንጀት ንብርብሮችን የማጥቃት አዝማሚያ ስላለው ፌስቱላ እንዲፈጠር እንደሚያደርግም ይነገራል፡፡
• አልሰሬቲቭ ኮላይተስ የሚባለው የአንጀት ቁስለት በሽታ ደግሞ ትልቁን አንጀት ወይም ፊንጢጣን ብቻ እንደሚያጠቃ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡
ከበሽታው ምልክቶች መካከልም÷ ተቅማጥ፣ ደም እና ንፍጥ የቀላቀለበት ሰገራ እና የሆድ ቁርጠት ይገኙበታል፡፡
የበሽታውን መከሰት እንዴት ማወቅ ይቻላል? • የደምና የሰገራ ምርመራ፣ ኢንዶስኮፒ ፣ የሆድ ራጅ እና ሲቲ ስካን እንዲሁም የሆድ አልትራሳውንድ ምርመራዎች በማድረግ የበሽታውን መከሰት ወይም አለመከሰት ማወቅ እንደሚቻልም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የአንጀት ቁስለት በሽታ ሕክምና • እንደ ህመሙ ደረጃ የሚሰጡ የተለያዩ ሕክምናዎች መኖራቸውንም ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡