የሀገር ውስጥ ዜና

በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ጥፋተኛ የተባሉ ግለሰቦች በጽኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጡ

By Amele Demsew

April 05, 2024

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ጥፋተኛ የተባሉ ግለሰቦች በ10 ዓመት ጽኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጡ፡፡

አብዱልሽኩር ኢማም ፣ኮንስታብል ሙህዲን አማን እና አብዱልአዚዝ ራህመቶ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ሪ. የወንጀል ህግ አንቀጽ 32(1) (ሀ) እና በሰው የመነገድና ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር 1178/2012 አንቀጽ 3 ንዑስ አንቀጽ 1 ሥር የተደነገገውን በመተላለፋቸው በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት በሕገ- ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል የቅጣት ውሳኔ ተላልፎባቸዋል።

ተከሳሾቹ በህገ-ወጥ መንገድ ሁለት ግለሰቦችን ዱባይ ለሥራ እናስቀጥራቸዋለን በማለት ከደቡብ ክልል ሃላባ ዞን ዌራ ወረዳ ወደ አዲስ አበባ በማስመጣት ለምርመራ፣ ለቪዛ፣ ለስልጠና እና ለፓስፖርት የሚውል ነው ብለው በአጠቃላይ 325 ሺህ ብር በመቀበላቸው ተገልጿል፡፡

በዚህም ጥር 10 ቀን 2014 ዓ.ም ከቀኑ 9 ሰዓት ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፍያ ወደ ዱባይ ጉዞ በማስመሰል ከሸኟቸው በኃላ አውሮፕላኑ ጅግጅጋ ሲያርፍ ከግብረ-አበሮቻቸው ጋር በመሆን እስከ ሶማሌ ላንድ ሀርጌሳ ከተማ እየተቀባበሉ ሌሎች የግል ተበዳዮችን ጨምሮ ከፍተኛ የአካል ጉዳት በማድረሳቸው ተጨማሪ ክፍያ ሲጠይቁ እንደነበሩ እና የግል ተበዳዮቹ አምልጠው ወደ ሀገር ቤት እንደተመለሱ የፍትህ ሚንስቴር ድንበር ተሸጋሪ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ ያስረዳል፡፡

ጉዳዩን የተመለከተው የወንጀል ችሎት ተከሳሾቹ ወንጀሉን በጋራ የፈጸሙት በመሆኑ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 84 ንዑስ አንቀጽ 1 (መ) መሠረት ሦስት የቅጣት ማቅለያ እና አንድ የቅጣት ማክበጃ በመያዝ በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ጥፋተኛ ናቸው ሲል የጥፋተኝነት ብይን ሰጥቷል፡፡

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የወንጀል ችሎት 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾችን እያንዳዳቸው በ10 ዓመት ጽኑ እስራትና በ11 ሺህ ብር፤ 3ኛ ተከሳሽን ደግሞ በ5 ዓመት ጽኑ እስራትና በ6 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ መወሰኑን የፌዴራል ፖሊስ መረጃ አመላክቷል፡፡