አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ አፍሪካ እና የካይዘር ችፍስ ተከላካይ መስመር እግር ኳስ ተጫዋች የሆነው ሉክ ፍሉርስ በጆሃንስበርግ ከተማ የመኪና ስርቆት በሚፈጽሙ ወንጀለኞች በጥይት ተመትቶ ህይወቱ ማለፉ ተገለጸ።
ክለቡ እንዳስታወቀው÷ የ24 ዓመቱ ተከላካይ በጆሃንስበርግ ከተማ ሆንዲው በተባለው ሰፈር መኪኒናውን ነዳጅ ለመሙላት እየተጠባበቀ በነበረበት ወቅት በተተኮሰበት ጥይት ህይወቱ አልፏል።
የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ቃል አቀባይ ማቬላ ማሶንዶ÷ ጥቃቱን መኪናውን ለመውሰድ በሚፈልጉ ወንበዴዎች መፈፀሙን ገልጸዋል።
የተጫዋቹን መኪና ይዘው የሸሹ ወንበዴዎችንም ለመያዝ ፖሊስ ክትትል እያደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ሉክ ፍሉርስ ከዚህ ቀደም ደቡብ አፍሪካን በመወከል በቶኪዮ ኦሊምፒክ በደቡብ አፍሪካ ከ23 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ስበስብ ውስጥ ተጫውቷል።
በደቡብ አፍሪካ የመኪና ስርቆት ወንጀል ከገዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱ የተገለፀ ሲሆን ወጣቱ ተከላካይ የዚህ ወንጀል ሰለባ መሆኑ መመላከቱን አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል፡፡