Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በ850 ወረዳዎች የሀገራዊ ምክክር የተሳታፊ ልየታ መጠናቀቁ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገር አቀፍ ደረጃ በ850 ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች የተከሄደው የተሳታፊ ልየታ መጠናቀቁን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጥበቡ ታደሰ በሰጡት መግለጫ÷ በ1ሺህ 300 ወረዳዎችና ከተማ አሥተዳደሮች የተሳታፊ ልየታ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ ውስጥም በ850 ወረዳዎችና ከተማ አሥተዳደሮች የተሳታፊ ልየታው መጠናቀቁን አመላክተው÷ የተሳታፊ ልየታ ለመሥራት የተያዘው ዕቅድም ከ70 እስከ 75 በመቶው ሥራ መገባደዱን አስረድተዋል፡፡

እስከ አሁን በተከናወነ የተሳታፊ ልየታ ሥራ ከ130 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች መለየታቸውን ጠቅሰው÷ 14 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በአጀንዳ መረጣ ቀጣይ መድረኮች ላይ እንዲሳተፉ ተመርጠዋል ብለዋል፡፡

በአፋር፣ አዲስ አበባ፣ጋምቤላ፣ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝ እና ሲዳማ ክልሎች የተሳታፊና የአጀንዳ ልየታ ሥራ መጠናቀቁንም አረጋግጠዋል፡፡

በዓለምሰገድ አሳዬ እና ሐይማኖት ወንድራድ

Exit mobile version