ጤና

የአሳማ ኩላሊት የተለገሰው ግለሰብ ከሆስፒታል አገግሞ መውጣቱ ተሰማ

By Meseret Awoke

April 04, 2024

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለመጀመሪያ ጊዜ የአሳማ ኩላሊት ንቅለ ተከላ የተደረገለት ግለሰብ ከሆስፒታል አገግሞ መውጣቱ ተሰምቷል፡፡

የኩላሊት ህመም በዓለም አቀፍ ደረጃ የብዙዎችን ሕልም ያጨለመና በርካቶችን ለህልፈት የዳረገ እና እየዳረገ የሚገኝ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ኩላሊት ሥራውን በአግባቡ ለመከወን ሲሰንፍ የኩላሊት ህመም ተከስቷል ይባላል፤ ህመሙ በጊዜ ከተደረሰበት በንቅለ ተከላ የሚታከም ቢሆንም ኩላሊት ማግኘት ግን ፈታኝ ጉዳይ ነው፡፡

አሁን ላይ በአሜሪካ ማሳቹሴትስ አጠቃላይ ሆስፒታል የተሰማው አዲስ ሕክምና የብዙዎችን ጭንቀት ወደ እፎይታ የቀየረና ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ተነግሯል፡፡

በሆስፒታሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓሳማን ኩላሊት ለሰው ልጅ በንቅለ ተካላ በመተካት ውጤታማ ሕክምና ማድረግ መቻሉ ተሰምቷል፡፡

የ62 ዓመቱ የዕድሜ ባለጸጋ ሪቻርድ ስሌይማን የኩላሊት ህመም እንዳለባቸውና በአፋጣኝ የኩላሊት ንቅለተከላ ማድረግ እንዳለባቸው ተነግሯቸው ዲያሊሲስ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡

ሆኖም ግለሰቡ የዓሳማ አካል ከአካላቸው ተስማምቶ ወደጤናቸው እንደሚመለሱ እርግጠኛ መሆን አልቻሉም ነበር ፤ይሁን እንጂ ሕክምናው በባለሙያዎች ታግዝ እውን ሆኗል፡፡

ከአሁን በፊት ተሞክሮ ያልተሳካው የዓሳማ ኩላሊት ንቅለ-ተከላ ጊዜው ደርሶ በዘርፉ ሊቆች ታግዞ የግለሰቡን ሕይዎት ማትረፉም በብዙዎች ዘንድ አግራሞትን ጭሯል፡፡

የንቅለ-ተከላ ሂደቱ አራት ሰዓታት እንደፈጀ የተናገሩት ሃኪሞች ፥ በአሁኑ ወቅት የዓሳማው ኩላሊት ከግለሰቡ ተዋህዶ በአግባቡ እየሰራ መሆኑን በማረጋገጥ ከሆስፒታል እንዲወጣ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ስሌይማን በበኩላቸው ፥ ህክምናው ተሳክቶ ወደቤቴ መሄዴ የሕይወቴ ትልቁ ደስታ ነው ማለታቸውን የዘገበው ቢቢሲ ነው፡፡

ታካሚውከአሁን በፊት ያደረጉት ንቅለተከላ ከሰው በተለገሳቸው ኩላሊት እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን ፥ ሆኖም ትንሽ ቆይቶ መስራት ማቆሙ ተነግሯል፡፡

ይሁን እንጂ ሕክምናው ሃኪሞች ባነሱት የዓሳማ ኩላሊት ንቅለ ተከላ ሙከራ መሳካቱ ነው የተነገረው፡፡

የዓሳማ ኩላሊት ንቅለ ተከላ ሕክምነው “እኔን ለመርዳት ብቻ ሳይሆን በሕይወት ለመትረፍ ንቅለ ተከላ ለሚያስፈልጋቸው በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ተስፋ የሚሰጥ መንገድ ሆኖ አይቸዋለሁ” ሲሉም ገልጸዋል።