የሀገር ውስጥ ዜና

የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ከተሞች ተመራጭ የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንዲሆኑ ያግዛል – ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

By Amele Demsew

April 04, 2024

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ከተሞች ተመራጭ የቱሪዝም እና የኢንቨስትመንት መዳራሻ እንዲሆኑ ለማድረግ ታቅዶ እተተገበረ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የአገልግሎቱ ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ÷ቀጣናውን በመሰረተ ልማት ለማስተሳሰር የኮሪደር ፕሮጀክት በኢትዮጵያ የተለያዩ ከተሞች ውስጥ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

የፕሮጀክቱ እሳቤ ከተሞች በቴክኖሎጂ የዘመኑ እንዲሆኑ እና ተመራጭ የቱሪዝም እና የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንዲሆኑ ለማስቻል ያለመ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ቀጣናውን በባቡር፣በውሃ ፣በአሌክትሪክ እንዲሁም ከመሰረተ ልማት ባለፈ በተለያዩ ፕሮግራሞች ለማዋሃድ በማሰብ የሚተገበር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የመዲናዋ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክትም በከተማዋ ቀደም ሲል የለሙ አካባቢዎችን ካልለሙት ጋር በመሰረተ ልማት በማስተሳሰር እንደ ስሟ ውብ እና ፅዱ ከተማ ለማድረግ ታስቦ የተደረገ መሆኑን ነው የገለፁት፡፡

ፕሮጀክቱ ንግድን እና የትራንስፖርት አገልግሎቶችን ቀልጣፋ ያደርጋል ያሉት ሚኒስትሩ÷ይህም የዜጎች ሕይወት እንዲሻሻል፣ከተሞች ለነዋሪዎች ምቹ እንዲሆኑ እና ሀገር እንድታድግ ያግዛል ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ የኮሪደር ልማቱ ቀጣናዊ ትስስርን በማፋጠን እና ዘላቂ እድገትን በማጎልበት የነዋሪዎችን ሕይወት በማሻሻል ረገድ ጉልህ ሚና የሚጫወት መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በሌላ በኩል ሚኒስትሩ በበጋ መስኖ ስንዴን የማምረት ፕሮግራም ያስገኘው ውጤት እየተሰራ ያለውን የምግብ ሉዓላዊነት ማረጋገጥ ስራ ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን እንደሚሳይ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ በተለይም በቆላማ አካባቢዎች በበጋ መስኖ ስንዴ የተገኘው ውጤት ዓለም አቀፍ እውቅና ማስገኘቱንም አስገንዝበዋል፡፡

ይህ ወቅት በአረንጓዴ አሻራ ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ፣በሌማት ትሩፋትና በሌሎች ሥራዎች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት እንዲኖር ለማስቻል የተሰራው ሥራ ውጤት ማሳየት የጀመረበት ጊዜ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በሚኪያስ አየለ እና አመለወርቅ ደምሰው