የሀገር ውስጥ ዜና

በሲዳማ ክልል በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ4 ሰዎች ሕይወት አለፈ

By ዮሐንስ ደርበው

April 03, 2024

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሲዳማ ክልል በደረሰ የትራፊክ አደጋ የአራት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን እና የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ አስታወቁ፡፡

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ ክፍል ዳይሬክተር ኮማንደር ከበደ ኬኔራ እንደገለጹት÷ አደጋው የተከሰተው ከሐዋሳ በቅርብ እርቀት በምትገኘው ሀዌላ ከተማ በተለምዶ ዶልፊን እና ቅጥቅጥ ተብለው የሚጠሩ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች በመጋጨታቸው ነው፡፡

የሲዳማ ክልል የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ደስታ ዳንቾ በበኩላቸው÷ የሁለቱ ሰዎች ሕይወት ወዲያውኑ ሲያልፍ ሁለቱ ደግሞ ሆስፒታል ከደረሱ በኋላ መሞታቸውን አረጋግጠዋል፡፡

በአሥራ አምስት ሰዎች ላይም ጉዳት መድረሱን እና በሐዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል የሕክምና ዕርዳታ እያገኙ እንደሚገኙ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል።

በመላኩ ገድፍ እና ጌታቸው ሙለታ