አዲስ አበባ፣ሰኔ 2 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ የ2019 የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ የሆኑትን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድን ለመሸለም ያሳለፈው ውሳኔ ትክክለኛነት ላይ ዛሬም ፅኑ እምነት እንዳለው ገለፀ።
ኮሚቴው አንዳንድ አካላት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የሰጠውን የኖቤል የሰላም ሽልማት “ለመሻር ዳግም እያጤነ ነው” ሲሉ ላናፈሱት ወሬ “ማረጋገጫዬን እሰጣለሁ በፊትም ሆነ አሁን ሽልማቱ መሰጠቱን ዳግም ለማጤን አላሰብኩም ወደፊትም ለማጤን ፍላጎት የለኝም” ብሏል።
ዛሬ በይፋ ባወጣው ደብዳቤ ይህ የኖቤል ሽልማት ኮሚቴ ሽልማት ከተበረከተ በኋላ መሻርን ፈፅሞ እንደማይፈቅድ አስታውቋል።
የኖቤል ሽልማት መሰጠት ከተጀመረ ከአሮፓውያኑ 1901 ጀምሮም የአንድም ተሸላሚ ሽልማት አለመሻሩንም ነው ያመለከተው።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ለሰላም እና ለዓለም አቀፍ ትብብር ላደረጉት ጥረት በተለይም ደግሞ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ለዓመታት የዘለቀው የድንበር የይገባኛል ውዝግብ በሰላም እንዲፈታ ተነሳሽነትን በመውሰዳቸው የ2019 የኖቤል የሰላም ተሸላሚ እንዳደረጋቸው ኮሚቴው መግለፁ የሚታወስ ነው።
ኮሚቴው በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ከኤርትራ ጋር ሰላም ለማምጣት ቃል መግባታቸውን በማስታወስ፥ የድንበር ኮሚሽን ውሳኔውን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በመቀበል ሀገራቱ አስመራ ላይ የሰላም ስምምነት እንዲፈራረሙ ማስቻላቸውን ነው ያነሳው።
በተጨማሪም ሁሉም ባለድርሻ አካለት በኢትዮጵያ፣ በምስራቅና በሰሜን ምስራቅ አፍሪካ አካባቢ ሰላም እና እርቅ እንዲመጣ ላደረጉት አስተዋፀኦ እውቅና ለመስጠትም እንደ ተሸለሙ ኮሚቴው መግለፁ አይዘነጋም።