Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በታይዋን በተከሰተ የመሬት መንቀጥቀጥ የ4 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በመቶዎች መቁሰላቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በታይዋን በተከሰተ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ የአራት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ 711 ሰዎች ላይ የመቁሰል አደጋ መድረሱ ተገልጿል፡፡
 
የታይዋን ምስራቃዊ የባህር ጠረፍ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ገደማ በሬክተር ስኬል 7 ነጥብ 5 በሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ መመታቱ ተመላክቷል፡፡
 
ንዝረቱም በዋና ከተማዋ ታይፒ እንዲሁም በደቡብ ጃፓን፣ በምስራቅ ቻይና እና በፊሊፒንስ መሰማቱ ተነግሯል።
 
በአደጋውም ቢያንስ የአራት ሰዎች ህይወት ማለፉ የተረጋገጠ ሲሆን 711 የሚሆኑት ደግሞ ቆስለዋል፡፡
 
በምስራቅ ሀውሊን ከተማ እና በዙሪያዋ ባሉ ተራራማ ገጠራማ አካባቢዎች የከፋ ጉዳት መድረሱ የተገለጸ ሲሆን በርካቶች መውጫ አጥተው እንደሚገኙ ተነግሯል፡፡
 
አደጋውን ተከትሎ ሱናሚ ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት እንዳለ በመግለጽ በታይዋን፣ በጃፓን እና በፊሊፒንስ ባለስልጣናት ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶ የነበረ ቢሆንም፤ በኋላ ላይ ማስጠንቀቂያው እንደተነሳ አልጀዚራ ዘግቧል።
Exit mobile version