አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኦቲዝም ስፔክትረም ዲስኦርደር (ኤኤስዲ) ወይም ኦቲዝም ከነርቭና አንጎል አሰራር ሂደት ጋር ግንኙነት ያለው የእድገት ችግር ነው፡፡
በዛሬው ዕለት የዓለም የኦቲዝም ቀን እየተከበረ ሲሆን፥ በዕለቱ ስለኦቲዝም ግንዛቤን በመፍጠር እና ስለህመሙ አነስተኛ ግንዛቤ ያላቸውን በማስፋት ቀኑ ተከብሮ ይውላል፡፡
ይህ ህመም ከሰዎች ጋር በሚደረግ ግንኙነት እና መስተጋብር ልዩነት ተለይቶ የሚታወቅ ሲሆን፥ ኦቲዝም ያለባቸው ሰዎች ብዙውን ጊዜ የተገደቡ እና ተደጋጋሚ ፍላጎቶችን ወይም ባህሪዎችን እንደሚያሳዩ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የኦቲዝም ምልክቶች በለጋ ዕድሜ ከአንድ እስከ ሁለት ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ በግልጽ የሚታይ ቢሆንም፥ ምልክቶች ቀደም ብለው ወይም በኋላ ሊታዩም ይችላሉ፡፡
• የመጀመሪያ ምልክቶች በቋንቋ ወይም በማህበራዊ እድገት ላይ ጉልህ ሆኖ የሚታይ መዘግየትን ሊያሳዩ ይችላሉ።
• ኦቲዝም ያለባቸው ህጻናት ከ36 ወራት ጀምሮ ስሜታቸውን የመግለጽ ወይም የሌሎችን ስሜት የመረዳት ችግር ሊገጥማቸውም ይችላል።
• ዕድሜያቸው እየጨመረ ሲመጣም የመናገር ችግር ሊኖርባቸው ወይም የንግግር ችሎታቸው በጣም ውስን ሊሆን ይችላል። በአንጻሩ ሌሎች የኦቲዝም ህጻናት የቋንቋ ችሎታቸውን ባልተመጣጠነ ፍጥነት ሊያዳብሩም ይችላሉ።
• ለእነሱ በጣም የሚያስደስት አንድ የተለየ ርዕስ ካለም በተለየ ሁኔታና የቃላት አጠቃቀም ሊገልጹት እንደሚችሉ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
• በተጨማሪም ጥቃቅን በሆኑ ነገሮችም ሊበሳጩና ተመጣጣኝ ያልሆነ ስሜት ያንጸባርቃሉ፡፡
• ጥቃቅን ነገሮች ላይ ትኩረት ማድረግ፣
• ለድምጾች፣ ሽታዎች እና ለጣዕም ለስሜት ህዋሳት ያልተለመዱ ምላሾች መስጠት፣ • ከልክ ያለፈ ፍላጎት • እንደ የሙዚቃ ችሎታ ወይም የማስታወስ ችሎታ ያሉ ልዩ ችሎታዎች ሊኖሩት ይችላል፡፡
አንዳንድ ኦቲዝም ያለባቸው ሰዎች የሚከተሉት ምልክቶች ሊታዩባቸው ይችላሉ፡-
• የዘገየ እንቅስቃሴ፣ ቋንቋ ወይም የግንዛቤ ችሎታ፣ • የሚጥል በሽታ፣ • የሆድ ድርቀት ወይም ተቅማጥ፣ • ከመጠን በላይ ጭንቀት፣ • ያልተለመደ የፍርሃት ደረጃ (ከተጠበቀው በላይ ወይም ያነሰ)፣ • ግትር፣ ትኩረት የለሽ ወይም ስሜት ቀስቃሽ ባህሪዎች፣ • ያልተጠበቁ ስሜታዊ ምላሾች፣ • ያልተለመዱ የአመጋገብ ልምዶች ወይም ምርጫዎች፣ • ያልተለመዱ የእንቅልፍ ሁኔታዎችና ሌሎች ምልክቶች ይጠቀሳሉ፡፡
የኦቲዝም ህክምና ለማድረግ ሦስት ዓይነት ዘዴዎች ጥቅም ላይ የሚውሉ ሲሆን፤ እነሱም የተለያዩ ምልከታዎችን/ህክምናዎችን ማድረግ፣ የዘር ምልከታዎች (ዲኤንኤን በመጠቀም) እንዲሁም የህመሙ ምልክት ግምገማዎች ማድረግ ናቸው፡፡
እስካሁን ለኦቲዝም መድሃኒት እንዳልተገኘለት ይነገራል፡፡ ሆኖም ለአንዳንድ ኦቲዝም ያለባቸው ሰዎች ደጋፊ ህክምናዎች የተሻለ ስሜት እንዲሰማቸው ወይም የተወሰኑ ምልክቶችን ለማስታገስ ሊረዷቸው እንደሚችሉ ከኽልዝላይን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ከእነዚህም መካከል የባህሪ፣ የጨዋታ፣ የሙያ፣ አካላዊ ሕክምና እንዲሁም የንግግር ሕክምና ይገኙበታል።