የሀገር ውስጥ ዜና

ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ በሻሸመኔ ከተማ ተካሄደ

By Amele Demsew

April 02, 2024

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ዓመታት የመጡ ለውጦችን የሚደግፍ ሰላማዊ ሰልፍ በሻሸመኔ ከተማ ተካሂዷል፡፡

የድጋፍ ሰልፉ ባለፋት ዓመታት በለውጡ መንግስት የመጡትን የማህበራዊ ፖሊቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን ለመደገፍ ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በለውጡ ዓመታት ላሳየው እመርታ ድጋፍ ለመግለጽ ያለመ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

የለውጡ መንግስት በግብርናው ዘርፍ ያሳየው እመርታ በተለይም ከዚህ ቀደም ያልተለመደውን የበጋ መስኖ ስንዴ ቆላማ በሚባሉ አካባቢዎች በመስራት ሃብትን በብልሃትና በእውቀት መጠቀም ምን እንደሆነ በተግባር ያሳየ መሆኑን የሰልፉ ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል፡፡

በማህበራዊ ዘርፍም ስራ አጦችን በውጭ ሀገራት ሳይቀር ስራ እንዲያገኙና ዜጎች በውጭ ሀገራት ክብር እንዲያገኙ የተጀመረው ስራ የሚበረታታ ነው ብለዋል ።

በፖለቲካም መንግስት በሀገሪቱ የሚፈጠሩ ችግሮችን በብልሃት ለመፍታት የሄደበት ርቀት የበሰለ ፖለቲካ በሀገራችን እየዳበረ መሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

‘’ለሰላማችን ዘብ እንቆማለን! ለውጡን እናጸናለን! የሚል መፈክር የያዙ ሰልፈኞች በተለይም የሀገራችንን አንድነት ሰላም ለማረጋገጥ የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን ያሉ ሲሆን ፥ ድላችንን እንጠብቃለን ፤ ለቀጣይ ስኬት በጋራ እንሰራለን!’’ ብለዋል።

በዚህ ሰልፍ ላይ ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም ፤ የወል ትርክት ለጠንካራ ሀገረመንግስት ግንባታ መሰረት ነው፤ ጠንካራ ኢትዮጵያ በህብረብሔራዊ ወንድማማችነት ላይ ትገነባለች ፤ በምክክርና መደማመጥ ሰላምን እናጸናለን ፤ የወል አቅማችንን በማጎልበት ኢኮኖሚያችንን በጽኑ መሰረት ላይ እንገነባለን ፤ ፈተና ብልጽግናችንን ከማረጋገጥ አይገታንም እንዲሁም ህብረብሔራዊነታችንን በማጠናከር ለሁሉም የምትመች ሀገር እንገነባለን የሚሉና ሌሎችም መፈክሮች በስፋት ተስተውለዋል፡፡

በጥላሁን ይልማ እና ለማ ተስፋዬ