አዲስ አበባ፣ ህዳር 30፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ የሰው ሀብት ልማት በ65 ነጥብ 8 በመቶ ሲያድግ፥ የእድሜ ጣራ ደግሞ በ14 ነጥብ 3 ዓመት ከፍ ማለቱን የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም አስታወቀ።
ድርጅቱ የአውሮፓውያኑ የ2019 የኢትዮጵያ ሰው ሀብት ልማት ሪፖርትን በዛሬው እለት ይፋ አድርጓል።
በሪፖርቱም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2000 ወዲህ በኢትዮጵያ የሰው ሀብት ልማት በ65 ነጥብ 8 በመቶ ማደጉን አስታውቋል።
እንዲሁም በሀገሪቱ ያለው የሰዎች የእድሜ ጣራም ከዚህ ቀደም ከነበረው በ14 ነጥብ 3 ዓመት ከፍ ማለቱን ነው ሪፖርቱ ያስታወቀው።
በኢትዮጵያ የሰው ሀብት ልማት በ65 ነጥብ 8 በመቶ ጭማሪ ቢያሳይም ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት አንጻር ሲታይ ግን ዝቅተኛ መሆኑን ሪፖርቱ አመላክቷል።
እንዲሁም የጾታ እኩልነትን ከማስጠበቅ አንጻርም ኢትዮጵያ ከ162 ሀገራት በ123ኛ ደረጃ ላይ መቀመጧንም ነው ሪፖርቱ ያመለከተው።
ኢትዮጵያ በትምህርት ዘርፍ ላይ አሁንም የበለጠ መዋእለ ንዋይ ማፍሰስ እንደሚጠበቅባትም ነው የተገለፀው።