አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የካናዳ ናያግራ ግዛት በፈረንጆቹ ሚያዝያ 8 የሚከሰተውን የፀሀይ ግርዶሽ ተከትሎ በታዋቂው የናያግራ ፏፏቴ ዙሪያ ብዙ ሰዎች ሊሰበሰቡ እንደሚችሉ በመገመት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል፡፡
በናያግራ ግዛት የአካባቢው ሊቀመንበር ጂም ብራድሌይ በሰጡት መግለጫ ÷የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታወጀው ብዙ ጥንቃቄዎች ማድረግ እንደሚገባ ከማሰብ የተነሳ መሆኑን ገልጸዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የነዋሪዎችን እና የጎብኚዎችን ጤና እና ደህንነት እንዲሁም ወሳኝ መሠረተ ልማቶችን ለመጠበቅ ብሎም ለማጠናከር እንደሚረዳም አመላክተዋል።
በካናዳ እና አሜሪካ ድንበር ላይ የሚገኙት ፏፏቴዎች ግርዶሹ በሚከሰትበት መስመር ላይ በመሆናቸው ብዙ ሰዎች ክስተቱን ለማየት ሲሉ ከወዲሁ በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙት የተፈጥሮ መስህቦች በአንዱ በሆቴሎች ለመቆየት አሊያም ቤት ለመከራየት ወደ ሥፍራው ሊጎርፉ እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡
የኦንታርዮ ከተማ ከንቲባ ጂም ዲዮዳቲ÷ በካናዳ በኩል የሚከሰተውን የፀሀይ ግርዶሽ ለመመልከት እስከ ዛሬ ወደ ሥፍራው ከመጡ ብዙ ሰዎች ሊገኙ ይችላሉ ሲሉ ተንብየዋል።
ዲኦዳቲ አያይዘውም በአጠቃላይ ሥፍራውን በዓመት ውስጥ ከሚጎበኙት 14 ሚሊየን ሰዎች ጋር ሲነፃፀር በዚህ ቀን ብቻ እስከ 1 ሚሊየን የሚደርሱ ሰዎች እንደሚታደሙ መገመታቸውን ሲጂቲኤን ዘግቧል።
በተጨማሪም ግዛቱ በዕለቱ መጨናነቆችን ለማስቀረት አንዳንድ መርሀ ግብሮቹን እና አገልግሎቶቹን እንደሚያሻሽልና እንደሚዘጋም አመላክቷል።