Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የ340 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ለተጎዱ ቆላማ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል እና የአየር ንብረትን ለመቋቋም የሚውል የ340 ሚሊየን ዶላር የብድር ድጋፍ አድርጓል።

ድጋፉ ከዓለም አቀፍ ልማት ማህበር (አይዲኤ) እንደተገኘና ከ3 ሚሊየን በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ የሚከሰተው ድርቅ በአብዛኛው የአርብቶ አደሮችን ህይወት ከባድ እንዳደረገው ይነገራል፡፡

ባለፉት ሶስት ዓመታት በቆላማው አካባቢ የተከሰተ ድርቅ ከፍተኛ የሆነ የእንስሳት ሞት ያስከተለ ሲሆን÷ በእንስሳቱ ላይ ጥገኛ የሆኑ በሚሊየን የሚቆጠሩ አርብቶ አደሮች ህይወት ላይም ተጽዕኖ ማሳደሩ ተመላክቷል።

አሁን ይፋ የተደረገው የቆላማ አካባቢዎች ኑሮን የመቋቋም ፕሮጀክት የአካባቢውን እምቅ አቅም በማሳደግ ለሀገራዊ እድገትና ድህነት ቅነሳ አስተዋፅዖ ያበረክታል ሲሉ የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ተወካይ ኦስማን ዲዮን ተናግረዋል።

የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ስርዓት መዘርጋት፣ የተቀናጀ አካባቢያዊ አስተዳደር እና የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም እንዲሁም የተረጋጋ ህይወት መምራትን የማስተዋወቅ ሥራዎች የፕሮጀክቱ ቁልፍ ተግባራት እንደሆኑ ማመላከታቸውን ከዓለም ባንክ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version