ቢዝነስ

ከ310 ሚሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ተያዙ

By Amele Demsew

March 30, 2024

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 310 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዙን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ከመጋቢት 13 እስከ 19 ቀን 2016 ዓ.ም በተደረገ ክትትል 189 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የገቢ እና 121 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር የወጭ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችበተለያዩ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች መያዛቸውን ነው ኮሚሽኑ ያስታወቀው፡፡

ከተያዙት ዕቃዎች መካከልም÷ አልባሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድኃኒት፣ የመዋቢያ ዕቃዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣ የመኪና መለዋወጫ፣ የምግብ ዘይት እና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች እንደሚገኙበት ተጠቅሷል፡፡

በተጠቀሰው የጊዜ ገደብም÷ ሞያሌ፣ ድሬዳዋ እና አዳማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች በቅደም ተከተላቸው 99 ሚሊየን፣ 77 ሚሊየን እና 50 ሚሊየን ብር ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን መያዛቸው ተመላክቷል፡፡

የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ የተያዙትም በፍተሻ፣ በበረራና በጥቆማ መሆኑን የኮሚሽኑ መረጃ አመላክቷል፡፡

በተጨማሪም የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹን ሲያዘዋውሩ ተገኝተዋል የተባሉ 19 ተጠርጣሪዎች እና አምስት ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል፡፡