Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የሞሪንጋ የጤና በረከቶች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሞሪንጋ በባህላዊ መንገድ በምግብነትና በመድሃኒትነት በማገልገል ዓለም አቀፋዊ እውቅና ያለው ተክል ነው፡፡

በሀገራችን “ሺፈራው” እየተባለ የሚጠራው ይህ ተክል በአሚኖ አሲድ፣ ቫይታሚን ኤ፣ ቫይታሚን ቢ1፣ ቢ2፣ ቢ3፣ ቢ6 እና በቫይታሚን ሲ የበለፀገ ነው።

በተጨማሪም÷ ካልሺየም፣ ፖታሺየም፣ ብረት፣ ማግኒዢየም፣ ፎስፈረስ እና ዚንክ ማዕድናትን ጨምሮ ለሰው ልጅ ከሚያስፈልጉት 20 ፕሮቲኖች መካከል 18ቱን ይዟል።

ሞሪንጋን ቅጠሉንና ዱቄቱን ሻይ ውስጥ በመጨመር እና በምንመገባቸው ምግቦች ላይ በመደባለቅ፣ ከሙቅ ውሃ ጋር ቀላቅሎ በመጠጣት ወዘተ ጥቅም ላይ ይውላል፡፡

የሞሪንጋ ተክል ሁሉም ክፍሎች የጤና ጥቅሞች ሊኖሩት እንደሚችሉ የሚታመን ቢሆንም ውጤታማ መሆኑን ለማረጋገጥ ተጨማሪ ምርምር እንደሚያስፈልግ ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡

ሞሪንጋ በተለያዩ ሀገራት በተለምዶ ተዓምረኛው ዛፍ፣ የከበሮ ዛፍ፣ የቤን ዘይት ዛፍ እና ሌሎች ስያሜዎች ተሰጥቶታል፡፡

የሞሪንጋ ተክል ከሚሰጣቸው ዋናዋና የጤና ጥቅሞች መካከል፦
•የቆዳንና የጸጉርን ጤንነት መጠበቅ፣
•እብጠትን ማከም፣
•የጉበት ጤንነትን መጠበቅ፣
• ካንሰርን መከላከል እና ማከም፣
• የሆድ ድርቀትን ማከም፣
• ምግብ ወለድ የባክቴሪያ ኢንፌክሽኖችን መዋጋት፣
• የሩማቶይድ አርትራይተስን መከላከል፣
• የስሜት እና የነርቭ ሥርዓት ህመሞችን ማከም፣
• የልብና የደም ዝውውር ሥርዓትን መጠበቅ፣
• የስኳር በሽታን ማከም፣
• የአስም በሽታን ማከም፣
• የኩላሊት ጠጠርን መከላከል፣
• ከፍተኛ የደም ግፊትን መቀነስ፣
•የአይን ጤናን ማሻሻል እና
•አኒሚያንና የሴል በሽታን ማከም የሚሉት የሚጠቀሱ መሆናቸውን የሜዲካል ኒዊስ ቱደይ መረጃ ያመላክታል፡፡

ሞሪንጋ እንደሌሎች መድሃኒቶች ወይም ተጨማሪ ምግቦች በምግብና መድሃኒት አስተዳደር ተቋማት ቁጥጥር ስለማይደረግበት በምግብነትም ሆነ በባህላዊ መድሃኒትነት ስንጠቀም ጥራቱ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም መረጃው ጨምሮ ገልጿል።

Exit mobile version