አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ስምንት ወራት ምርመራ ከተደረገላቸው 10 ሚሊየን ሰዎች ውስጥ 3 ነጥብ 2 ሚሊየን የሚሆኑት በወባ በሽታ መያዛቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የሰዎችን እንቅስቃሴ ተከትሎ በሁሉም አካባቢዎች በሽታው ሊኖር ይችላል ያለው ሚኒስቴሩ÷ በተለይ በኦሮሚያ፣ አማራ፣ በደቡብ ምዕራብ እና በደቡብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ስርጭቱ ከፍተኛ መሆኑን ገልጿል፡፡
በሚኒስቴሩ የወባና ሌሎች ትንኝ ወለድ በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዴስክ ሀላፊ ጉዲሳ አሰፋ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳሉት÷ አሁን ላይ በሳምንት እስከ 70 ሺህ ሰዎች በበሽታው እየተያዙ ነው፡፡
ጥር ወር ላይ ከነበረው ከፍተኛ የበሽታ ስርጭት አንጻር ሲታይ በአሁኑ ወቅት ከ5 እስከ 10 በመቶ መቀነስ እያሳየ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ ግን በዚህ ሊቀጥል አይችልም ብለዋል።
በተለይ የቀጣይ የክረምቱን ዝናብ ተከትሎ የበሽታው ስርጭት ከፍ ሊል እንደሚችልም አስጠንቅቀዋል።
አሁን ላይ እንደ ሀገር በቂ የወባ መድሃኒት መሰራጨቱንና መድሃኒት እየተገዛ መሆኑንም ጠቅሰው፤ ስርጭቱ ላይ ካልሆነ በቀር የመድሃኒት ዕጥረት እንደሌለ አረጋግጠዋል፡፡ በአጠቃላይ በሽታውን ለመከላከል የኬሚካል ርጭት፣ የክትትልና የቁጥጥር ስራዎችን ጨምሮ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም አክለዋል፡፡
በመሳፍንት እያዩ