ዓለምአቀፋዊ ዜና

ቻይና 6 ስፍራዎችን በዩኔስኮ የዓለም መልክዓ ምድር ቅርስነት አስመዘገበች

By Mikias Ayele

March 28, 2024

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና ስድስት ስፍራዎችን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የዓለም መልክዓ ምድር ቅርስነት ማስመዝገቧን አስታውቃለች፡፡

የዩኔስኮ ስራ አስፈፃሚ ቦርድ በዓለም መልክዓ ምድር ቅርስ ዘርፍ ተጨማሪ 18 ስፍራዎች እንዲመዘገቡ ያፀደቀ ሲሆን፤ በአጠቃላይ ከ48 ሀገራት በዚህ ዘርፍ የተመዘገቡት ስፍራዎች ቁጥር ወደ 213 ከፍ ማለቱ ተገልጿል፡፡

 

 

 

ከተመዘገቡት መልክዓ ምድሮች ውስጥ በቻይና ሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ ጂሊንግ ግዛት ውስጥ የሚገኘው የቻንግባይሻን ተራራ አስደናቂ የመሬት ቅርጾችን እና የተለያዩ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ቅሪቶችን መያዙ ተመላክቷል፡፡

በተራራው ከ1 ሺህ ዓመታት በፊት የተፈጠረ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ የሚገኝበት እንደሆነም ተነግሯል።

በተጨማሪም በሁቤ ግዛት የሚገኘው ኤንሺ ግራንድ ካንየን ዋሻ፣ በጋንሹ ግዛት የሚገኘው ሊንሺያ፣ በፉጂያን ግዛት የሚገኘው ሎንግያን፣ በጂያንግዚ ግዛት የሚገኘው ዉጎንግሻን እንዲሁም በጊዙ ግዛት ውስጥ የሚገነው ዝንጂ መልክዓ ምድሮች በዩኔስኮ ተመዝግበዋል፡፡

ፓርኮቹ የተለየ የተፈጥሮ ቅርፅ የያዙ ታሪካዊ ስፍራዎች መሆናቸውን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡