አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አርጀንቲናዊው ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ በአሁኑ ወቅት ለኢንተርሚያሚ እየተጫወተ ይገኛል።
ከወራት በኋላ 37ኛ ዓመቱን የሚይዘው ሊዮኔል ሜሲ ከቢግ ታይም ፖድካስት ጋር ባደረገው ቃል ምልልስ፤ የእድሜው መግፋት በእግርኳስ ህይወቱ ላይ የሚያመጣው ጫና እንደሌለ ተናግሯል።
በመሆኑም በእግር ኳስ ሜዳ ላይ ስለሚያስመዘግበው ስኬት እንጂ ስለ ዕድሜው አስቦና ተጨንቆ እንደማያውቅ ተናግሯል፡፡
“በእግርኳስ እዝናናለሁ፣ ባለሁበት ቡድን እና በነገሮች ሁሉ ደስተኛ ነኝ፣ አሁን ላይ ስራዬ ላይ ስለማተኮር እንጂ በየትኛው እድሜዬ ላይ እግርኳስን ማቆም እንዳለብኝ አስቤ አላውቅም” ሲል ተናግሯል፡፡
ከእግርኳስ ጡረታ የምወጣበትን ጊዜ መተንበይ አልችልም ያለው ሜሲ፤ ኳስ መተው ያለብኝ ትክክለኛው ጊዜ ሲደርስ የማልፀፀትበትን ውሳኔ እወሰናለሁ ብሏል፡፡
ሜሲ በእግርኳስ ህይወቱ 10 የላሊጋ እና 4 የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን ከካታላኑ ክለብ ባርሴሎና ጋር ማሳካት ችሏል፡፡
በተጨማሪም ለሀገሩ አርጅንቲና ብሄራዊ ቡድን ተሰልፎ የዓለም ዋንጫ ያነሳው ሜሲ የ8 ጊዜ የባሎን ዲ ኦር ሽልማትን ማሸነፉ ይታወቃል፡፡
ብዙውን ጊዜ በእግርኳስ ታሪክ ውስጥ ተጨዋቾች በ30ዎቹ መጨረሻ ላይ ኮከብነታቸውን ለማስቀጠል የሚቸገሩ ቢሆንም አርጀንቲናዊው ሜሲና ፖርቱጋላዊው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ጥንካሬያቸውን ጠብቀው መቆየት ችለዋል።
ሜሲ በ36 ዓመቱ ከአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን ጋር የዓለም ዋንጫ ማንሳት የቻለና የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች ለመሆን የበቃ እንደሆነ ይታወሳል።