አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ባለፉት የለውጥ ዓመታት በኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፎች የተከናወኑ ስራዎች የህዝቡን ኑሮ እያሻሻሉ መሆኑን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ገለጹ።
የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀይሉ አዱኛ ÷በክልሉ ከለውጡ በፊት በግብርናና በኢንዱስትሪ ላይ ብቻ ታጥሮ የቆየውን የኢኮኖሚ መስክ በተለያየ መንገድ ማስፋት መቻሉን አመልክተዋል።
በተለይም የግብርና ዘርፍ የክልሉ መንግስት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት፣ ለውጪ ገበያ የሚውሉ ምርቶችን በስፋት ማምረትና የስራ እድል ፈጠራ ምንጭ እንዲሆን ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል።
በዚህም ግብርናውን ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ በተደረገ ጥረት በክልሉ አብዛኛው አካባቢዎች በዓመት ሁለትና ሶስት ጊዜ ማረስ ተችሏል ያሉ ሲሆን÷ የክልሉ መንግስት ለግብዓት አቅርቦት እና ግብርናውን በቴክኖሎጂ ለማገዝ ሰፋፊ ስራዎች መስራቱንም ጠቅሰዋል።
በተሰራው ስራም የክልሉ አርሶ አደር ኑሮ ላይ ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን አስታውሰው፤ በእነዚህ ዓመታት አገሪቷ ስንዴን ወደ ውጪ መላክ እንደትችል ክልሉ የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።
ከመደበኛ የግብርና ስራ ጎን ለጎን በከተማ ግብርና፣ በማዕድን ልማትና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍም አመርቂ ውጤቶች መገኘታቸውን ተናግረዋል።
በከተማ ግብርና የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ፣ የስራ እድል ለመፍጠርና ኢንቨስትመንትን ከመሳብ አንጻርም ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውን አስረድተዋል።
በተመሳሳይ በማህበራዊ ልማት ዘርፍ በትምህርትና በጤና ዘርፍ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በህዝቡ ኑሮ ላይ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ማሳረፍ እንደተቻለ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በዚህም ባለፉት ሶስት ዓመታት ብቻ በህብረተሰብ ተሳትፎ ከ15 ሺህ በላይ ‘ቡኡራ ቦሩ’ የተሰኙ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል።
በትምህርት ቤት ምገባ ረገድም በክልሉ በተያዘው 2016 ዓ.ም 5 ነጥብ 3 ሚሊየን ተማሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ አንስተው የ’ኢፋ ቦሩ’ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ግንባታ የተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በጤና ዘርፍም ባለፉት ጥቂት ዓመታት 1 ሺህ 500 የጤና ተቋማት የተገነቡ ሲሆን÷ የሁለተኛ ትውልድ የጤና ኬላዎች ግንባታ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።