የሀገር ውስጥ ዜና

ሌሴቶ በግብርናው ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር ለመሥራት እንደምትፈልግ ገለጸች

By Amele Demsew

March 26, 2024

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሌሴቶ መንግሥት በግብርናው ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ ለመሥራት ፍላጎት እንዳለው በኢትዮጵያ የሌሴቶ አምባሳደር ንቺዩዋ ሴኬቴ ገለጹ፡፡

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ከአምባሳደር ንቺዩዋ ሴኬቴ ጋር በግብርናው ዘርፍ በጋራ መሥራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

በዚሁ ወቅትም ሚኒስትሩ ባለፉት አምስት ዓመታት መንግሥት ለግብርናው ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ ዘርፉን ለማዘመን እያከናወነ ያለውን ጥረት አስረድተዋል፡፡

በዚህም÷ በስንዴ ልማት፣ በእንስሳትና ዓሣ ሃብት ልማት፣ በሌማት ትሩፋት፣ በአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብሮች የተገኙ ስኬቶችን ማብራራታቸውን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

አምባሳደር ንቺዩዋ ሴኬቴም የኢትዮጵያ መንግሥት ለግብርናው ዘርፍ የሰጠውን ትኩረት አድንቀው÷ በዘርፉ ሌሴቶ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ ለመሥራት እንደምትፈልግ አረጋግጠዋል፡፡