Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የሴቶችን የውሳኔ ሰጪነት አቅም ለማሳደግ የተጀመረው ጥረት መቀጠል አለበት – ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሴቶችን የአመራርነትና የውሳኔ ሰጪነት አቅም ለማሳደግ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ አስገነዘቡ፡፡

በፕሬዚዳንት ጽ/ቤት፣ ዩ ኤን ውሜን እና ቢል ኤንድ ሚሊንዳ ጌትስ ፋውዴሽን አስተባባሪነት ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ለተወጣጡ ሴቶች በስድስት ዙሮች ሲሰጥ የነበረው “የመካከለኛ አመራር ሴቶች ስልጠና” የማጠቃላይ መርሐ-ግብር ተካሂዷል፡፡

ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ በመርሐ-ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ በከፍተኛ አመራርነት የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ጥረቶች መደረጋቸውን አንስተዋል፡፡

በስድስት ዙሮች የተሰጠው ስልጠናም የሴቶችን የከፍተኛ አመራርነት አቅም ማሳደግ፣ ወደ መሪነት እንዲመጡ የመደገፍና ማበረታታት ዓላማ ያለው ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ስልጠናው መካከለኛ ሴት አመራሮች በእውቅትና ክኅሎት እንዲገነቡና ከአቻ ሴቶች ጋር ልምድ እንዲለዋወጡ ማስቻሉንም ጠቅሰዋል፡፡

በመሆኑም የሴቶችን የአመራርነትና የውሳኔ ሰጪነት አቅም ለማሳደግ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ነው ያሉት።

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)÷ የተሰጠው ስልጠና ተተኪ ሴት አመራሮችን ለማፍራት፣ የአመራርነትና ውሳኔ ሰጪነት አቅማቸውንም ለማሳደግ ያለመ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በሀገር ዕድገት፣ ልማትና ለውጥ ሴቶች ግንባር ቀደም ተሳታፊ እንዲሆኑ በመንግስት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

የስልጠናው ተሳታፊዎች በበኩላቸው÷ ከስልጠናው በመሪነት ሚና ጠቃሚ ልምድና እውቀት ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

በስድስት ዙሮች በተካሄደው ስልጠና ከመንግስት፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና ከግሉ ሴክተር የተወጣጡ ከ180 በላይ ሴቶች ተሳትፈዋል፡:

Exit mobile version