የሀገር ውስጥ ዜና

የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ወገኖች ላይ መሥራት እንደሚገባ ተመላከተ

By Amele Demsew

March 24, 2024

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሁላችንም በምንችለው ሁሉ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ወገኖች ልንሠራ ይገባል ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ አስገነዘቡ፡፡

ዓለም አቀፉ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ቀን እና “መጋቢትን ከዲቦራ ጋር” መርሐ-ግብር በወዳጅነት ዐደባባይ ተከብሯል።

ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር÷ ሁላችንም በምንችለው ሁሉ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች ላይ መሥራት አለብን ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

ዲቦራ ፋውንዴሽን ተስፋ ነው የሰጠን ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸውን ከደገፍናቸው እና ዕድሉን ከሰጠናቸው ነገ የሀገር ተስፋ መሆን ይችላሉ ብለዋል።

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ወገኖችን እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ ጉዳዩ በአካል ጉዳተኞች ሕግ ላይ እንዲገባ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

በቅድስት አባተ