የሀገር ውስጥ ዜና

የግብርና ሚኒስቴር በቦንጋ ከተማ ያስገነባውን 5 የአረጋውያን ቤቶች አስረከበ

By Shambel Mihret

March 23, 2024

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የግብርና ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማቱ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቦንጋ ከተማ በ16 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ወጪ ያስገነቡትን አምስት የአረጋውያን ቤቶች አስረከቡ።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) በርክክቡ ወቅት፤ ዜጎች በተለያየ ምክንያት ለችግር ሲጋለጡ ካለን በማካፈል እና በመርዳት የጀመርነውን ስራ አጠናክረን ማስቀጠል አለብን ብለዋል።

የግብርና ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት ላደረጉት የቤት ዕድሳት ስራ አመስግነው፤ ባህል ሆኖ እየመጣ ያለውን የተቸገሩትን የመርዳት ልምድ ማጠናከርና ማስፋፋት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው እስካሁን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደሀገር በከተማና በገጠር ከ100 ሺህ በላይ ቤቶች ተገንብተው ለአረጋውያን ማስረከብ መቻሉንም ጠቁመዋል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) ለአረጋውያኑ ቤት ግንባታ 16 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉን ገልጸዋል።

የቤት ግንባታው ተሰርቶ እስከተጠናቀቀበት ዕለት ድረስ ለአረጋውያኑ የቤት ኪራይ እና ሌሎች ተያያዥ መጪዎችን በማመቻቸት ሲደገፉ እንደነበርም መግለጻቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ጠቁሟል።