አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሩሲያ መዲና ሞስኮ አቅራቢያ በምትገኘው ክሮከስ ከተማ በሙዚቃ ኮንሰርት እየተካሄደበት በነበረ አዳራሽ ውስጥ ከተፈፀመው ጥቃት ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ 11 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ።
በጥቃቱ የሞቱት ሰዎች ቁጥር እስካሁን 143 መድረሱ ተነግሯል።
በድርጊቱ እጃቸው እንዳለበት ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉት ውስጥ አራቱ ታጥቀው በአዳራሹ ውስጥ ግድያ የፈጸሙ እንደሆነ ሮይተርስ ዘግቧል።
ጥቃቱን በመፈጸም አንድ ታጣቂ ቡድን ሀላፊነቱን እንደሚወስድ የገለጸ ቢሆንም፤ ሩሲያ ድርጊቱ ከዩክሬን ጋር ከገባችበት ቀውስ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ገልጻለች።
የዩክሬን ፕሬዚዳንት አማካሪ ሚካይሎ ፖዶሊያክ ድርጊቱ ከሀገራቸው ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።
ነገር ግን ጥቃቱን በመፈጸም ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል አራቱ በሩሲያ-ዩክሬን ድንበር አካባቢ መያዛቸውን የሩሲያ የደህንነት አገልግሎት ተቋም አስታውቋል።
ራሺያን ታይምስ እንዳስነበበው ታጣቂዎቹ የታገተ ሰው ለማስለቀቅ ወይም ሌላ አላማ ይዘው ወደ ከተማዋ አልገቡም ይልቁኑ ሰለማዊ ዜጎችን መግደል አላማቸው ነበር ብለዋል፡፡
የሩሲያ ባለስልጣናት ድርጊቱ የሽብር ጥቃት ሊሆን እንደሚችል ጠቅሰው፤ በጉዳዩ ላይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
የደረሰውን ጥቃት አስመልክቶ በሩሲያ ብሔራዊ ቴሌቪዥን መልዕክት ያስተላለፉት ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፤ የተፈጸመው ጥቃት ግልጽ የሽብር ድርጊት መሆኑን ተናግረዋል።
ጠላቶቻችን ሊከፋፍሉን አይችሉም ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ የአደጋ አገልግሎትና የልዩ አገልግሎት ሰራተኞች ጉዳቱን ለመቀነስ ላደረጉት ጥረት ምስጋና አቅርበዋል።
ሩሲያ የድርጊቱ ፈጻሚዎች ተገቢውን ቅጣት እንዲቀጡ የምታደርግ መሆኗን አመልክተዋል።