የሀገር ውስጥ ዜና

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ አጋጥሞ የነበረው ችግር የሳይበር ጥቃት አለመሆኑ ተመላከተ

By Amele Demsew

March 22, 2024

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መጋቢት 7 ቀን 2016 ዓ.ም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ ያጋጠመው ችግር ከሲስተም ማሻሻያ ትግበራ ጋር የተያያዘ እንጂ የሳይበር ጥቃት አለመሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር አስታወቀ፡፡

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የአሥተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ በሰጡት መግለጫ÷ በተደረገ ምርመራ ባንኩ ለሚቃጡበት የሳይበር ጥቃቶች አስቀድሞ መከላከል የሚያስችል አቅም እንዳለው ተረጋግጧል ብለዋል፡፡

ከሰሞኑ ያጋጠመው ችግር እንዲከሰት ምክንያት የሆኑ ጉዳዮች በምርመራ መለየታቸውን ጠቁመዋል፡፡

በዚሁ መሠረትም ባንኩ በሞባይል ሲስተሙ ላይ ባደረገው የማሻሻያ ሥራ የተከሰተ እንጂ የሳይበር ጥቃት አይደለም ብለዋል፡፡

ባንኩ የሲስተም ጃር ፍይል ሶርስ ኮድ (JAR Files Source Code) ወስዶ ባደረገው ምርመራ የፕሮግራሚንግ ቅደም ተከተል ወይም ሎጂካል ፍሰቱ የተዛባ ሆኖ ማግኘቱንም ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም ሲስተሙ ገንዘብ የሚያወጡ የባንኩ ደንበኞች ገንዘብ ሲያወጡ መቀነስ የነበረበትን መጠን ሳይቀንስና ቫላንስ ለመሥራት ወይም ለማመዛዘን አመቺ ሁኔታ ሳይፈጥር ክፍያ ይፈፅም እንደነበር መረጋገጡን አንስተዋል፡፡

በመሆኑም ባንኩ የሳይበር ጥቃት እንደደረሰበት የሚናፈሰው መረጃ የተሳሳተ መሆኑን አስገንዝበው÷ በቀጣይም ተጨማሪ ምርመራዎችና የፎረንሲክ ሥራዎችን በማከናወን ውጤቱ ለሕብረተሰቡ እንደሚገለጽ አመላክተዋል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደርም በኢትዮጵያ ላይ የሚቃጡ የሳይበር ጥቅቶችን ለመከላከል እና የተቋማትን ደኅንነትን ለማስጠበቅ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

በምስክር ስናፍቅ