ጤና

የስትሮክ አጋላጭ ሁኔታዎችና ምልክቶች

By Feven Bishaw

March 23, 2024

 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለያዩ ምክንያቶች ድንገት ደም ወደ አዕምሮ መሄዱን ሲያቆም ወይም ደግሞ በአንጎል ውስጥ ደም ሲፈስ የሚከሰት ድንገተኛ ህመም “ስትሮክ” ይባላል::

ከ50 በመቶ በላይ ስትሮክ የሚከሰተው በደም ግፊት ሲሆን÷ ከፍተኛ የሆነ ደም ግፊት በቁጥጥር ውስጥ ሳይውል ረጅም ጊዜ ሲቆይ አዕምሮ ውስጥ ያለ ደም ሥር ሊበጠስ ይችላል፤ በዚህም የደም መፍሰስ ስትሮክ ያስከትላል።

እንዲሁም ከፍተኛ ደም ግፊት ሲኖር ደም ስሮች ላይ የረጋ ደም ይፈጠራል፤ በዚህ ወቅት ወደ አንጎል የሚሄድ ደም ስር የመዘጋት ስትሮክ ያጋጥማል።

ስኳርና ልብ ከመሳሰሉ በሽታዎች ጋር ተያይዞ በሚመጡ ችግሮች፣ ከተክለ-ሰውነት ጋር ያልተመጣጠነ ውፍረት፣ በቂ አካላዊ እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ ጤናማ ያልሆነና ቅባት የበዛበት ምግብ አዘውትሮ መመገብ፣ ጭንቅላት ላይ የሚደርስ አደጋ፣ አልኮል አዘውትሮና ከመጠን በላይ መውሰድ፣ አደንዛዠ እጽ፣ ሲጋራ፣ ሺሻና ጫት መጠቀም ለስትሮክ ህመም አጋለጭ ምክንያቶች ናቸው፡፡

እንዲሁም የእድሜ መግፋት፣ የማይገታ ጭንቀት፣ ጫና፣ ማህበራዊ ጫና (ጦርነት፣ ድርቅ፣ ችግር፣ ረሃብ ወዘተ) ለስትሮክ ህመም ተጋላጭነትን ይጨምራል። ወንዶች ከሴቶች በበለጠ በስትሮክ የመጠቃት እድላቸው ከፍተኛ ነው።

ስትሮክ ያለምንም ቅድመ ምልክት ሊከሰት የሚችልበት አጋጣሚ እንዳለውና ጉዳት እንደደረሰበት የአእምሮ ክፍል የስትሮክ ህመም ምልክት እንደሚለያይም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መረጃ ያመላክታል፡፡

በዚህም እጅና እግርን የሚቆጣጠረው የአእምሮ ክፍል ላይ ደም ሥር ከተዘጋ ወይም ደም ከፈሰሰ እጅ፣ እግር ሥራቸውን መሥራት ያቆማሉ፣ በከፊል ሰውነት ሽባ ወይም ፓራላይዝድ ይሆናል።

በተመሳሳይ ንግግርን የሚቆጣጠረው የአንጎል ክፍል ላይ ጉዳት ከደረሰ መናገር ሊያዳግት ወይም ንግግሩ ሊቆራረጥ፣ ሊኮላተፍ፣ ሊጎተት ወዘተ ይችላል፤ እንዲሁ እይታን የሚቆጣጠር የአንጎል ክፍል ላይ ጉዳት ከደረሰ እይታን ሊያግድ ይችላል።

ከዚህ ባሻገር ሚዛንን ስቶ መንገዳገድ፣ ማዞር፣ ራስን መሳት፣ ከፍተኛ የሆነ ራስ ምታት፣ መርሳት፣ መደንዘዝ ወዘተ ምልክቶች ካሉ በተመሳሳይ ስትሮክ ሊሆን ስለሚችል በፍጥነት ወደ ሆስፒታል መሄድ እንደሚገባ የህክምና ባለሙያዎች ያሳስባሉ።

በስትሮክ የተጠቃ ሰው በአራት ሰዓት ከ30 ደቂቃ ውስጥ ሆስፒታል ከደረሰ ሕይወቱን ማትረፍ እና ሊደርስበት ከሚችል ከባድ የጤና ችግር ለመታደግ እድሉ ከፍተኛ ሲሆን÷ ወደ ሆስፒታል መሄድ በዘገዩ ቁጥር ከስትሮክ ጋር ተያይዘው የሚፈጠሩ ተጓዳኝ ህመሞች የመፈጠር እድላቸው ይጨምራል።

በመሆኑም ከላይ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ታካሚው ሆስፒታል ከደረሰ ለሁሉም አይነት የስትሮክ ህመሞች በአስቸኳይ የሚሰጡ ልዩ ልዩ ህክምናዎች አሉ።