የሀገር ውስጥ ዜና

80 የፋይናንስ ተቋማት የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ አባል ሆነዋል ተባለ

By Amele Demsew

March 22, 2024

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) እስካሁን 80 ያህል የፋይናንስ ተቋማት የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ አባል መሆናቸው ተገለፀ።

የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ የግንዛቤ ፈጠራና የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ምክትል ገዥና የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ የቦርድ ሰብሳቢ ሰለሞን ደስታ በበመድረኩ ላይ እንዳሉት÷ የተረጋጋ የፋይናንስ ዘርፍ ለመፍጠር የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ መጠናከር አለበት።

ለዚህም የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ወደ ስራ መግባቱን ጠቅሰው÷ ተቋሙ በዓለም 148ኛ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ መሆን ችሏል ብለዋል።

በተቋቋመ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለውጤታማነት የሚያገለግሉት የተለያዩ መመሪያዎችን ማዘጋጀትና ሌሎች በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ስራ አስፈፃሚ ደሳለኝ አምባው (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

በዚህም ለፋንናንስ ተቋማት የዓረቦን ክፍያዎችን መሰብሰብ የሚያስችሉ፣ ለውርስ ስራ የሚያስፈልጉ እና ሌሎች መመሪያዎች ይገኙበታል ብለዋል።

በእስካሁኑ ሂደትም 31 የግል እና የመንግስት ባንኮች፣ 49 ማይክሮ ፋይንስ ተቋማት አባል መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ 6 ወራት ውስጥ ከ 2 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ ከአባል ፋይናንስ ተቋማት የዓረቦን ክፍያ መሰብሰቡንም ስራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።

የዓረቦን መጠኑን እስከ በጀት ዓመቱ መጠናቀቂያ ድረስ 6 ቢሊየን ለማድረስ መታቀዱንም ጠቁመዋል፡፡

የመድረኩ አላማም የተቋሙን የህግ ማዕቀፍ፣ አላማና ተግባር፣ እስካሁን የተከናወኑ ስራዎችን ለመገምገም ታሳቢ ያደረገ ነው ተብሏል።

በተጨማሪም ተቋሙን ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችሉ ምክረ ሀሳቦችን ለመሰብሰብና የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ለማሳደግ ያለመ መሆኑ ተመላክቷል።

በሳሙኤል ወርቃየሁ እና ሰለሞን ይታየው