የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የነጻ ንግድ ቀጠና ስምምንት የ6 ሺህ እቃዎችን የታሪፍ ዝርዝር አጸደቀች

By Amele Demsew

March 19, 2024

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የነጻ ንግድ ቀጠና ስምምንት የ6 ሺህ እቃዎችን የታሪፍ ዝርዝር ማጽደቋን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።

ለስምምንቱ ተግባራዊነትም ኢትዮጵያ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጓን እና የስምምነቱን ማስተግበሪያ ስትራቴጂ እያዘጋጀች መሆኑን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል።

በቅርቡም ኢትዮጵያ ልክ እንደሌሎቹ የሙከራ ንግድ ልውውጥ እንደጀመሩ የአፍሪካ ሀገራት ከተመረጡ ሀገራት ጋር የሙከራ ንግድ ልውውጥ ለመጀመር የሚያስችላትን የስትራቴጂ ዝግጅት እያደረገችም ነው ብለዋል።

በዚህም የ6 ሺህ እቃዎች ታሪፍ ምን መሆን እንዳለበት እና 90 በመቶ የገቢ እና ወጪ ምርቶች የታሪፍ ሁኔታ ዝርዝር እንደቀረበም ነው የገለጹት፡፡

በሌላ በኩል እንደየሀገራቱ ፖሊሲ በፍጥነት ከታሪፍ ነጻ መሆን በማይችሉ የ7 በመቶ ምርቶች እና ኢትዮጵያ ስትራቴጂያዊ በምትላቸው እንዲሁም በዚህ ማዕቀፍ እንዳይካታቱ በምትፈልጋቸው የ3 በመቶ ምርቶች ላይ ዝርዝር አቅርባ ማጸደቋ ተገልጿል።

ይህ የአፍሪካ የነፃ ንግድ ቀጠና ስምምንት ታዲያ ወደ ሙሉ ትግበራ ሲሸጋገርም በዓለም ግዙፉ የነጻ ንግድ ቀጠና ስምምነት በመሆን የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 ግብ የሆነውን በኢኮኖሚ የጠነከረች አህጉር እዉን ለማድረግ እንደሚያግዝ ተመላክቷል፡፡

በመራኦል ከድር