የሀገር ውስጥ ዜና

ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን የተወካዮች መረጣ አጠናቀቀ

By Amele Demsew

March 19, 2024

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሲያካሂድ የቆየውን የተወካዮች መረጣ አጠናቋል፡፡

ኮሚሽኑ በክልሉ በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ ተሳታፊ የሚሆኑ ተወካዮችን ከየካቲት 19 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ከየማህበረሰብ ክፍሉ ሲያስመርጥ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

የክልሉ የተወካዮች መረጣ 12 ዞኖችን በማካተት ሲከናወን የቆየ ሲሆን 9 ሺህ 300 የሚሆኑ ተሳተፊዎችን የሂደቱ አካል ማድረጉ ተገልጿል፡፡

በዚሁ ክንውን ተሳታፊዎች በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ የሚወክሏቸውን ተወካዮች ከመምረጣቸው ባሻገር በየወረዳቸው እና በየማህበረሰብ ክፍሎቻቸው ገንቢ ውይይቶችን ማድረጋቸው ተጠቁሟል፡፡

ኮሚሽኑ በቀጣይ ሳምንት በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የተወካዮች መረጣን ማከናወን እንደሚቀጥልም የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡