ጤና

ባለፉት 2 ወራት ከ9 ሺህ በላይ ሰዎች በኩፍኝ ተይዘዋል- ኢንስቲትዩቱ

By Shambel Mihret

March 18, 2024

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ ከ9 ሺህ 500 በላይ ሰዎች በኩፍኝ በሽታ መያዛቸውን የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

በ10 ክልሎች በሚገኙ 91 ወረዳዎች በሽታው መኖሩን በኢንስቲትዩቱ በክትባት የምንከላከላቸው በሽታዎች ቅኝትና ምላሽ ቡድን አስተባባሪ ሚኪያስ አላዩ ገልጸዋል፡፡

በዚህም ባለፉት ሁለት ወራት ከ9 ሺህ 500 በላይ ሰዎች በኩፍኝ ተይዘዋል፤ የ63 ሰዎች ሕይወትም አልፏል ብለዋል፡፡

የወረርሽኙ ሥርጭት በስፋት ከሚስተዋልባቸው ክልሎችም÷ ኦሮሚያ፣ አማራ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ቀዳሚዎቹ መሆናቸውን ነው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተናገሩት፡፡

የኩፍኝ ወረርሽኝን ለመከላከል መደበኛ ክትባትን ማጠናከርና ክትባት ያልወሰዱ ሕፃናትን የመከተብ ሥራ መቀጠሉን ጠቅሰው÷ በሁለት ወራትም ከ2 ሚሊየን በላይ ሕፃናት መከተባቸውን አስታውቀዋል፡፡

ባለፉት ሦስት ዓመታት ከ57 ሺህ በላይ ሰዎች በኩፍኝ መያዛቸውን እና ከ460 የሚልቁት መሞታቸውን አስታውሰዋል፡፡

በዙፋን ካሳሁን