Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በመዲናዋ 2 ነጥብ 3 ሚሊየን ነዋሪዎች የጤና መድህን ተጠቃሚ ሆነዋል ተባለ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ 2 ነጥብ 3 ሚሊየን ነዋሪዎች የማህበረሰብ ዓቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን የከተማ አስተዳደሩ ጤና ቢሮ አስታውቋል፡፡

በቢሮው የማህበረሰብ ዓቀፍ ጤና መድህን ዳይሬከተር ኢብራሂም ተካ ለፋና ብሮድካስቲን ኮርፖሬት እንዳሉት፤ ማህበረሰቡ ስለ ጤና መድህን ያለው ግንዛቤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመሆኑ የተጠቃሚዎች ቁጥር እያደገ ይገኛል፡፡

በዚህም በ2015 ዓ.ም 2 ነጥብ 1 ሚሊየን የነበረው የማህበረሰብ ዓቀፍ ጤና መድህን የተጠቃሚዎች ቁጥር በአሁኑ ወቅት ከ2 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ መድረሱን ጠቁመዋል፡፡

ይህም በማህበረሰብ ዓቀፍ ጤና መድህን መካተት አለባቸው ከሚጠበቁት ህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ 93 በመቶ እንደሆነ አመልክተዋል።

ከተማ አስተዳደሩ መክፈል ለማይችሉ 480 ሺህ ዜጎች ሙሉ ክፍያ እና በፌደራል ደረጃ የጤና አገልግሎት ለሚያገኙት ደግሞ ድጎማን ጨምሮ በአጠቃላይ 600 ሚሊየን ብር ድጎማ ማድረጉንም ነው የገለጹት፡፡

በተለይ የጤና መድህን ተጠቃሚዎች መድሃኒቶችን በመንግስት የጤና ተቋማት እንዲያገኙ ለማስቻል ተቋማት ግብዓት እንዲያሟሉ እገዛ እየተደረገ እንደሚገኝም አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም በጤና ተቋማት የማይገኙ መድሃኒቶችን ከከነማ ፋርማሲ እና ከግል ፋርማሲዎች እንደ አማራጭ እንዲጠቀሙ ስምምነት ተደርጓልም ብለዋል ፡፡

በመሳፍንት እያዩ

Exit mobile version