አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ሕብረት በአባል ሀገራቱ እንዳይንቀሳቀሱ ከታገዱ የሩሲያ ንብረቶች የሚገኘውን ትርፍ ዩክሬንን ጦር መሳሪያ ለማስታጠቅ ሊያውል መሆኑ ተሰምቷል፡፡
ሩሲያና ዩክሬን በፈረንጆቹ 2022 የካቲት ወር ላይ ጦርነት ሲጀምሩ ምዕራባውያን ሀገራት የሩሲያ ማዕከላዊ ባንክ ንብረት የሆነውን 300 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ አግደዋል።
የጀርመኑ ቻንስለር ኦላፍ ሾልስ ከፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮንና ከፖላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ተስክ ጋር በበርሊን በጋራ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፥ ከታገዱ የሩሲያ ንብረቶች የሚገኘውን ትርፍ ለዩክሬን ጦር መሳሪያ ግዢ እንጠቀማለን።
የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌይን ባለፈው ወር ከታገዱ የሩሲያ ንብረቶች የሚገኘውን ትርፍ ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ለመግዛት እንዲውል ሃሳብ ማቅረባቸው የሚታወስ ነው ።
ሞስኮ በንብረቶቿ ላይ የሚወሰደው ማንኛውም እርምጃ “ስርቆት” እንደሆነ በተደጋጋሚ አስጠንቅቃለች፡፡
መሰል እርምጃ መውሰድም ዓለም አቀፋዊ ሕግን የሚጻረር እና የምዕራባውያን ምንዛሪ፣ የዓለም የፋይናንስ ስርዓትና የዓለም ኢኮኖሚን የሚያዳክም መሆኑን አበክራ መግለጿን አርቲ ዘግቧል፡፡