Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የአጀንዳ አሰባሰብ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ላይ ውይይት እያካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአጀንዳ አሰባሰብ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያካሄደ ነው።

በውይይት ማስጀመሪያ መርሃ-ግብሩ ላይ የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፤ ሀገራዊ ምክክር መግባባት ላይ ባልተደረሰባቸው ጉዳዮች መግባባት ላይ እንዲደረስ ኢትዮጵያውያን ተወያይተው የጋራ መፍትሔ እንዲያስቀምጡ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ በወረዳዎች ደረጃ ሲያከናውን የቆየውን የተሳታፊ ልየታ ሥራዎች በተሳካ ሁኔታ ማካሄዱን ገልፀው፤ ሀገራዊ ምክክር ለሀገረ-መንግሥት ግንባታ ታላቅ መሠረት የሚጥል ነው ብለዋል።

ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም ለምክክሩ ወሳኝ እና ተከታታይ የሆኑ ሥራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ገልጸው፤ ለዚህም በርካታ ተባባሪ አካላት መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

ለበርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎች በሀገራዊ ምክክር ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫዎች መሰጠታቸውንም አስታውቀዋል።

የሀገራዊ የምክክር ሂደት ለትውልድ የምትመች ሀገር ለማስተላለፍ እንደሚረዳ መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በዛሬው ዕለትም የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የአጀንዳ አሰባሰብ ሂደት ማስጀመሪያ የአሰራር ስርዓት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያካሄደ ነው ብለዋል።

እየተካሄደ በሚገኘው የውይይት መድረክ ሚኒስትሮች፣ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ ከሁሉም ክልሎች የተወከሉ ባለድርሻ አካላት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

 

Exit mobile version