አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ በሃማስ የቀረበውን የተኩስ አቁም እና የእስረኞች ልውውጥ ሃሳብ ውድቅ በማድረግ በደቡባዊ የጋዛ ከተማ ራፋህ የእስራኤል ጦር ለማካሄድ ያቀደውን ወታደራዊ ዘመቻ ማፅደቃቸው ተነግሯል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት በሰጠው መግለጫ የእስራኤል ጦር ንፁሐንን ከአካባቢው ለማስለቀቅ እና ዘመቻውን ለማካሄድ ዝግጁ መሆኑ ተገልጿል።
ቀደም ብሎ ሃማስ በኳታር እና በግብፅ አሸማጋይነት ከእስራኤል ጋር እስረኞችን ለመለዋወጥ እና የእስራኤል ጦር ጋዛን ለቆ መውጣትን ያካተተ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ያለውን ዕቅድ አቅርቦ እንደነበር ተመላክቷል፡፡
የፍልስጤም ታጣቂዎች ያቀረቡት የስምምነት ዕቅድ እንደሚያሳየው፤ ተዋጊ ሴቶችን ጨምሮ ሌሎች እስራኤላውያን ሴቶችን፣ ልጆችን፣ አረጋውያንን እና የታመሙ ታጋቾችን መለዋወጥ ከ700 እስከ 1 ሺህ የሚደርሱ ፍልስጤማውያን እስረኞችን ነፃ ያደርጋል፡፡
አንድ ጊዜ የእስረኞች ልውውጥ ከተጠናቀቀ በኋላም ዘላቂ የተኩስ አቁም ድርድር ለማድረግ እንደሚዘጋጅም ነው የሃማስ ዕቅድ የሚዘረዝረው፡፡
ይሁን እንጂ እስራኤል ሃማስን ያልተገባ ጥያቄ በመጠየቅ ወቅሳ ዕቅዱን ውድቅ ማድረጓን አርቲ ዘግቧል፡፡
በትናንትናው ዕለትም ኔታኒያሁ እስራኤል ሃማስን የማጥፋት ተልዕኮዋን ለማጠናቀቅ ያላትን ቁርጠኝነት በድጋሚ አረጋግጠዋል።19:44